የሀይል እርምጃን የሚያነሳሱና የሚያበረታቱን ይዘቶች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ አስተዋጾ እናድርግ!

twitter verification

ነሐሴ 15፣ 2015 ዓ.ም

ምንም እንኳን ባለፉት አመታት በሀገራችን ለተከሰተው ምስቅልቅልና መጠነ ሰፊ ጉዳት ላደረሱ ግጭቶች ያደሩና ያልተፈቱ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ዋነኛ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸው እውነት ቢሆንም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ አሉታዊ ይዘቶች ችግሮችን በማባባስና በማቀጣጠል አይነተኛ ሚና ስለመጫዎታቸው በተደጋጋሚ ተነስቷል።

የሀይል እርምጃን የሚያነሳሱና የሚያበረታቱን ጨምሮ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ አሉታዊ ይዘቶች መቻቻልን፣ የዜጎች ውይይትና ምክክርን፣ መከባበርና መግባባትን ከማቀጨጫቸውም በተጨማሪ ግጭቶች እንዲባባሱና እንዲወሳሰቡ ግለሰቦች ካለፍርድ እንዲገደሉና አካላዊ ጉዳት እንዲደርስባቸው አስተዋጾ ስለማድረጋቸው በሰፊው ተነግሯል።

እንዲህ ባሉ አሉታዊ ይዘቶች ምክንያት በቤተሰባቸውና በቅርብ ዘመዶቻቸው ላይ ሞትና አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትህ ለማግኘት ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤቶች መውሰድ መጀመራቸውም በተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች መዘገባቸው የሚታወቅ ነው።

ሆኖም በአሉታዊ ይዘቶች ሳቢያ ከደረሱ ጉዳቶች ተምሮ እራስን ከማረቅ ይልቅ አንዳንዶች ይህን አጥፊ ድርጊት በስፋትና በደረጃ መልኩ ሲያስቀጥሉ መመልከት የተለመደ ሆኗል።

ከሰሞኑ በአማራ ክልል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተገናኘም የሀይል እርምጃን የሚያነሳሱና የሚያበረታቱ በርከት ያሉ አሉታዊ ይዘቶች ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመጋራት ላይ መሆናቸውን በቀላሉ መታዘብ ይቻላል።

የግለሰቦችን ስም፣ የቤተሰብ አባላት፣ ፎቶ፣ አድራሻ ወዘተ በመዘርዘር እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚያነሳሱና የሚያበረታቱት እነዚህ ይዘቶች ሀሳብ በነጻነት ከመግለጽ መብት ጋር የሚጣረሱ ከመሆናቸው ባለፈ ካለፍርድ በሰዎች ላይ አካላዊ ጥቃት እንዲፈጸም እና የመንጋ ፍትህን እንዲሰፍን የሚያደርጉ ናቸው።

የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞችም ለእንዲህ ያሉ ይዘቶች ቦታ እንደሌላቸው በፖሊሲያቸው በግልጽ አስቀምጠዋል።

ስለሆነም የሀይል እርምጃን የሚያነሳሱና የሚያበረታቱን ጨምሮ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ አሉታዊ ይዘቶች የሚያደርሱትን የከፋ ጉዳት ለመቀነስ ሁላችንም ሀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።

እንዲህ ያሉ ይዘቶችን የሚያጋሩ አካውንቶችንና ገጾች ባለመከተል፣ በመቃወም እንዲሁም ሪፖርት በማድረግ ተደራሽነታቸውን በእጅጉ መቀነስ እንችላለን!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::