የተቋማትን ስም እና አርማ በመጠቀም የሚጻፉ ሀሠተኛ ደብዳቤዎችን ለመለየት የሚረዱ ነጥቦች

የተቋማትን ስም እና አርማ በመጠቀም የሚጻፉ ሀሠተኛ ደብዳቤዎችን ለመለየት የሚረዱ ነጥቦች

ሚያዝያ 9፣ 2016

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የትላልቅ ተቋማትን ስም እና አርማ በመጠቀም የተጻፉ ሀሠተኛ ደብዳቤዎች በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያ ገጾች መሰራጨታቸውን ተመልክተን ነበር። ከነዚህም መካከል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) እና በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እንደተጻፉ ተደረገው የተሰራጩትን ሀሠተኛ ደብዳቤዎች መጥቀስ ይቻላል።

ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሱት ደብዳቤዎች በግልጽ የሚታዩ ግድፈቶች የሚታዩባቸው ቢሆኑም ቀላል የማይባሉ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ደጋግመው ሲያጋሯቸው ተስተውሏል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ደብዳቤዎቹ ሀሠተኛ መሆናቸውን የሚገልጹ የማስተባበያ መልዕክቶችን በኦፊሴላዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ማጋራታቸውን ተመልክተናል።

እንዲህ ያሉ የተቋማት ስምን እና አርማን በመጠቀም የሚጻፉ ደብዳቤዎች ለሀሠተኛና ለተዛቡ መረጃዎች የማጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ስለሆነ ከማመናቸንና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ቆም ብለ ማሰብና መመርመር ይጠበቅብናል። ሀሠተኛ ደብዳቤዎችን ለመለየትም የሚከተሉት ነጥቦች ይረዱናል

በመጀመሪያ በማህበራዊ ሚዲያ የምናያቸውን ደብዳቤዎች ከማመናችናን መልሰን ከማጋራታቸን በፊት ደብዳቤዎቹን ያጋራውን ግለሰብ ወይም ገጽ ማንነት፣ ታማኝነት እንዲሁም ፍላጎት ማጤን ይኖርብናል።

ደብዳቤው የተቋም ስምንና አርማን በመጠቀም የተጻፈ ከሆነ በተጠቀሰው ተቋም የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶች ወይም ድረገጾች መጋራታቸውን ማየት ጠቃሚ ይሆናል። በተጨማሪም ተቋሙን በስልክ፣ በኢሜል ወይም በውስጥ መልዕክቶች መጠየቅ ስለ ደብዳቤው ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ይረዳል።

የደብዳቤውን ቅርጽና ይዘት በሚገባ መፈትሽም ስለትክክለኛነቱ መረጃ ሊሰጠን ይችላል። ለምሳሌ ደብዳቤው የተጻፈበት የፊደል አይነት (font type) ፣ የፊደል መጠን (font size) ፣ የተቋሙ አርማ አቀማመጥ፣ የደብዳቤ ቁጥር፣ ቀን፣ ማህተም ፊርማ፣ ስም ወዘት በጥንቃቄ ማስተዋል እንዲሁም ቀደም ካሉ የተቋሙ ደብዳቤዎች ጋር ማመሳከር እውነታውን ለማወቅ ይረዳል። ለማመሳከሪያነት የሚጠቅሙ በተቋሙ የተጻፉ ቀደም ያሉ ደብዳቤዎችን ከየተቋማቱ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶች ወይም ድረገጾች በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።

የመረጃ አጣሪ ተቋማት ደብዳቤውን በተመለከተ ያጋሩት የተጣራ መረጃ መኖሩን መፈተሽ አልያም ጥቆማ መስጠት እውነታውን ለማወቅ ሌላው አማራጭ መንገድ ነው።

የተቋማትን ስምና አርማ በመጠቀም የሚሰራጩ ደብዳቤዎች ለሀሠተኛ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችንና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ጥንቃቄና ማጣራት እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::