ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ‘እረፍት የለሹ የኢትዮጵያው ጠ/ሚር አዲስ አበባን በፍጥነት እያዘመኗት ነው’ ብሎ የሰራው ዘገባ የለም

ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት 'እረፍት የለሹ የኢትዮጵያው ጠ/ሚር አዲስ አበባን በፍጥነት እያዘመኗት ነው' ብሎ የሰራው ዘገባ የለም

ሚያዝያ 20፣ 2016

ከ6,890 በላይ ተከታታዮች ያሉት እና ‘CHERBOLE’ የሚል ስያሜ የሚጠቀም የትዊተር አካውንት ከዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ድረ-ገጽ የተወሰደ የሚመስል አንድ የስክሪን ቅጂ (ስክሪንሾት) በትናትናው ዕለት ማጋራቱን ተመልክተል።

በስክሪን ቅጂው ላይም ‘Ethiopia’s restless prime minister is modernising Addis Ababa too fast’ ወይም ወደ አማርኛ ሲተረጎም ‘እረፍት የለሹ የኢትዮጵያው ጠ/ሚር አዲስ አበባን በፍጥነት እያዘመኗት ነው’ የሚል ርዕስ ይነበባል። በተጨማሪም ዝቅ ብሎ ‘Abiy Ahmed is making the city too clean for Africa’ የሚል ተቀጥያ ርዕስ ይነበባል።

በዚህ ስክሪን ቅጂ ላይ ጽሁፉ እ.አ.አ ሚያዚያ 25/2024 ዓ.ም መታተሙን የሚገልጽ ቀን አመላካች መስመር (dateline) ይታያል።

ከላይ የተጠቀሰውን ስክሪን ቅጂም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መልሰው ሲያጋሩት አስተውለናል።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ስክሪን ቅጂው ኤዲት ተደርጎ የተሰራ (doctored) መሆኑን አረጋግጧል።

ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ከላይ በተጠቀሰው ቀን አዲስ አበባን የተመከተ ዘገባ ያስነበበ ሲሆን የተጠቀመው ርዕስ ግን ‘The historic heart of Addis Ababa is being demolished’ የሚል ወይም ሲተረጎም ‘የአዲስ አበባ ታሪካዊ መሀል ቦታ እየፈረሰ ነው’ የሚል ነበር። በተቀጥያ ርዕስነት ደግሞ ያስነበበው ጽሁፍ ‘Abiy Ahmed is imposing his vision on Ethiopia’s capital’ የሚል ነበር።

መፅሄቱ በዚህ ዘገባው ‘የኮሪደር ልማት’ በተባለው እንቅስቃሴ ሰለባ የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችን አነጋግሮ ሰፋ ያለ መረጃ አጋርቶ ነበር።

በተጨማሪም ኤዲት በተደረገው ስክሪን ቅጂ የሆሄያትና የስርዐተ ነጥቦች አቀማመጥ ግድፈቶች በግልጽ እንደሚታዩ አስተውለናል።

ትክክለኛውን የመጽሔቱን ዘገባ ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ማግኘት ይቻላል: https://www.economist.com/middle-east-and-africa/2024/04/25/the-historic-heart-of-addis-ababa-is-being-demolished?utm_medium=social-media.content.np&utm_source=twitter&utm_campaign=editorial-social&utm_content=discovery.content

መረጃውን አጋርተው የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት ምናልባትም ስክሪን ቅጂው ሀሰተኛ መሆኑን ከተረዱ በኋላ በሚመስል መልኩ ቆይተው እንዳጠፉ መመልከት ችለናል።

ኤዲት ተደርገው የሚሰራጩ ስክሪን ቅጂዎች ለሀሠተኛ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችንና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢውን ጥንቃቄና ማጣራት እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::