“ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ እና ከዳሽን ባንክ ጋር ያለው ግንኙነት እስካሁን አልተቋረጠም”— የጤና ሚኒስቴር

Ministry of health rejected allegations of termination of agreement with Gojo bridge housing ጤና

መጋቢት 26፣ 2016

“በተያዘው በፕሮግራም መሰረት በዓመት አራት ጊዜ እጣ መውጣት እያለበት እስካሁን 2 ጊዜ ብቻ ወጥቷል”— የጤና ባለሙያዎች

ከሰሞኑ “ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተፈራረመውን የጤና ዘርፍ ሰራተኞች ቤት ግንባታ ስምምነት አፍርሷል፤ ቤት ለማግኘት ክፍያ የፈጸሙ የጤናው ዘርፍ ሰራተኞችም ተጭበርብረዋል” የሚሉና ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን እንዲያጣራ የሚጠይቁ መልዕክቶች ከተከታታዮቻችን ደርሰውናል።

የጤና ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ ቼክ ባደረሱት ተከታታይ መረጃ የከፈሉት ብር ይመለሳል የሚል መረጃ ሲዘዋወር እንደተመለከቱና ይህም ማለት ማህበሩ ፈርሷል ብለው እንዲያስቡ እንዳረጋቸው ጠቁመዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ አክለውም የጎጆ ዕጣ በተያዘው በፕሮግራም መሰረት በዓመት አራት ጊዜ መውጣት እያለበት እስካሁን 2 ጊዜ ብቻ ወጥቷል፣ በውል ስምምነቱ መሰረት በየ 3 ወሩ ነው ዕጣ ይወጣል ቢልም በ ውሉ መሰረት ዕጣ አልወጣም እንዲሁም ችግሮች እንኳን ቢኖሩ እነዚህ ችግሮች ሲፈጠሩ ወቅታዊ መረጃ ለተመዝጋቢዎች አልተሰጡም የሚሉ ቅሬታዎች ቀርበዋል።

የጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ ሰራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክትን በተመለከተ ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ እና ዳሽን ባንክ ጋር የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርሞ የመጀመሪያ ዙር እጣ ማውጣት ስነ ሰርዓት የተካሄደው ሰኔ 2015 ላይ ነበር።

በስነ ሰርዓቱም 200 ጤናው ዘርፍ ሠራተኞች የመጀመርያ ዙር የዕጣ እድለኞች ሲሆኑ ዕጣ  የማውጣት ሂደቱ በየሶስት ወሩ እንደሚቀጥልና እየሰፋ እንደሚሄድም ተጠቁሞ ነበር። ይህ መረጃም በወቅቱ በሚኒስቴሩ የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ ተጋርቶ ነበር፡ https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid02PnHVv2sH6DiS4B6m3H72FzPTVitoq2k2GBKEcPQyytBMPkZfZFDFctwHqBTWjB9El&id=100064567187444&mibextid=qC1gEa

ይሁን እንጂ “ሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመው ስምምነት ፈርሷል” የሚለውን መረጃ መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ቼክ ከጤና ሚኒስቴር እና ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት አድርጓል።

በጤና ሚኒስቴር የጤና ዘርፍ ሰው ሀብት ልማት ማሻሻያ መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ አሰግድ ሳሙኤል ጉዳዩን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ቼክ መረጃ የሰጡ ሲህን ‘በሁለቱ ተቋማት መካከል የተፈረመው ስምምነት ፈርሷል’ የሚለው መረጃ ሀሰት መሆኑን ነግረውናል።

“ጤና ሚኒስቴር ከጎጆ እና ከዳሽን ባንክ ጋር ያለው ግንኙነት እስካሁን አልተቋረጠም። ያንን የሚያደርግ ከሆነ ጤና ሚኒስቴር በባለሙያው በኩል ነው የቆመው” ያሉት አቶ አሰግድ፤ “ማንኛውም በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ነገር ባለሙያው ላይ ማንኛውም አይነት ችግር የሚፈጥር ከሆነ (ጤና ሚኒስቴር) በፍጹም ዝም ብሎ የሚያይበት ነገር አይኖርም። ስለዚህ የመግባቢያ ስምምነቱ እስካሁን አልተቋረጠም” ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ጋር ስምምነት ሲፈጽም የተቋሙን ህጋዊ ሰነዶችን ተመልክቶ መሆኑን የሚናገሩት ስራ አስፈጻሚው ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ፤ ዳሽን ባንክና ጤና ሚኒስቴር የተፈራረሙት ስምምነት አላማ 10 ሺህ ቤቶችን በ10 አመት ገንብቶ ለመጨረስ እንደሆነም ነግረውናል።

ባጠቃላይ ከ8000 በላይ ሰራተኞች የፕሮግራሙ አካል መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አሰግድ፤ እስካሁን በሁለት ዙሮች 400 የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች በጋራ የማህበር ቤት እንዲገነቡ እጣ እንደወጣላቸውም ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ “እጣዎቹ ከወጡ በኋላ ችግር የሆነው ከመሬት አስተዳደር፤ ከአዲስ አበባ ማህበራት ማደራጃ ጋር ተያይዞ የተወሰኑ የአሰራር ለውጦች ተደረጉ። ከተማ ውስጥ ያለው ከመሬት ጋር ተያይዞ ያለው ችግርም የሚታወቅ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ያንን ማኔጅ ለማድረግ በየጊዜው የሚያወጣቸው አዳዲስ ህጎች አሉ። እነሱ (ሂደቱን) አፌክት አድርገውታል” ብለዋል።

ስለዚህም እጣ የወጣላቸው እድለኞች በሚፈለገው ጊዜ ግንባታ ያለመጀመራቸውን በመጥቀስ “ትልቁ እኛም የገመገምነው ችግር አሁን ባልኩት ዉስጣዊም ዉጫዊም ችግሮች፤ ጎጆም ጋር ባለው ግንባታው ዘግይቷል የሚል ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ጤና ሚኒስቴር የጤናው ዘርፍ ሰራተኞችን ለማበርታትና ለማትጋት ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ በተጨማሪ ሌላ የመኖሪያ ቤት ማግኛ አማራጮች ላይ እየሰራ መሆኑንም አቶ አሰግድ ሳሙኤል ለኢትዮጵያ ቼክ ነግረዋል።

በሌ በኩል ጉዳዩን በተመለከተ የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግን አስተያየት ለማግነት ለዋና ስራ አስኪያጁ አቶ አለማዉ ጋሪ ብንደዉልም ለጊዜው መረጃ ማግኘት አልቻልንም።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::