ትዊተር በአዲሱ የአካውንት ማረጋገጫ የተገበረው የክፍያ ስርዐት

twitter verification

መጋቢት 18፣ 2015 ዓ.ም

በማህበራዊ ሚዲያ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የጥላቻ ንግግሮች እንዲሁም የማታለልና የማጭበርበር ድርጊቶች ከሚሰራጩባቸውና ከሚፈጸምባቸው ዘዴዎች መካከል ተመሳስለው የሚከፈቱ ሀሠተኛ አካውንቶች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ይህን ችግር ለመቅረፍ የአካውንት ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክት መስጠትን እንደቀዳሚ መፍትሄነት ሲጠቀሙበት መቆየታቸው ይታወቃል። በዚህ ረገድ ትዊተር ይህን አገልግሎት በቀዳሚነት በመጀመር የሚጠቀስ ነው።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም በአብዛኛው ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ትላልቅ ተቋማት ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል።

ሆኖም ባለጸጋው ኢሎን መስክ ትዊተርን መግዛቱን ተከትሎ ይህ አገልግሎት በክፍያ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን የመክፈል አቅም ያለው ማንኛውም የትዊተር ተጠቃሚ የአካውንት ማረጋገጫ ማግኘት የሚችልበት አሰራር ተዘርግቷል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በነጻ የአካውንት ማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክት የተሰጣቸው ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ለማስቀጠል ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 1 ቀን 2023 ዓ.ም ቀደም ብለው ወደ ክፍያ ስርዐቱ መግባት እንዳለባቸው ኩባንያው ከቀናት በፊት አስታውቋል።

አዲሱ የትዊተር አካውንት ማረጋገጫ ስርዐት አካውንቶችን በሶስት የሚከፍል ሲሆን ለግለሰቦች ሰማያዊ (Blue)፣ ለተቋማት ወርቃማ (Golden) እና ለመንግስትና ለበይነ መንግስታት (multilateral organisations) ባለስልጣናትና ተቋማት ግራጫ (Grey) ቀለም ያለው ምልክት ያቀርባል።

ሰማያዊ የአካውንት ማረጋገጫ ምልክት የሚፈልጉ ግለሰቦች በየወሩ 8 የአሜሪካን ዶላር አካባቢ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። ወርቃማ የአካውንት ማረጋገጫ ምልክት ለጊዜው በሙከራ ላይ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎቱን ለማግኘት በወር 1000 ዶላር መክፈል እንደሚያስፈልግ ትዊተር አስታውቋል። ግራጫ ምልክት የሚፈልጉ የመንግስትና የበይነ መንግስታት ባለስልጣናትና ተቋማት ትዊተር ያዘጋጀውን ቅጽ መሙላት ይጠበቅባቸዋል።

ምንም እንኳን አዲሱ የትዊተት አሰራር የመክፈል አቅምንና በውጭ ምንዛሬ ለመክፈል መቻልን የሚጠይቅ ቢሆንም የአካውንት ማረጋገጫ ምልክቶች ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን እንዲሁም የማታለልና የማጭበርበር ድርጊቶች ከመከላከል አንጻር ከሚኖራቸው አይተኬ ሚና አኳያ አቅም ያላቸው የትዊተር ተጠቃሚዎች ወደ ስርዐቱ ቢገቡ መልካም ነው እንላለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::