በቲክቶክ የሚጋሩ ሀሠተኛ እና የተዛቡ ይዘቶችን ለመለየት የሚረዱ ነጥቦች

Tips to identify fake and distorted content shared on TikTok

ነሐሴ 18፣ 2015 ዓ.ም

በተዛቡ መረጃዎች ስርጭት ዙሪያ የሚሰራው ኒውስጋርድ (NewsGuard) የተሰኘው የጋዜጠኞች ቡድን ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት ባለው የፈረንጆች ዓመት በቲክቶክ ፍለጋ (tiktok search) አማካኝነት ከሚመጡ ቪዲዮዎች መካከል 20% የሚሆኑት ሀሰተኛ ወይም የተዛባ ይዘት ያላቸው መሆናቸው አስነብቧል።

እነዚህ ሀሰተኛ ወይም የተዛባ ይዘት ያላቸው ቪዲዮዎችም በፍለጋ ውጤቶች ቅደም ተከተል ከላይ መገኘታቸው አስታውቋል።

ቲክቶክን በመጠቀም ሀሰተኛና የተዛቡ ይዘቶች ከሚሰራጩባቸው መንገዶች መካከልም ከአውድ ውጭ የተወሰዱ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ድምጾች፣ የተቀናበሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ድምጾች፣ የጽሁፍ ማብራሪያዎች፣ ተሰናስነው የሚቀርቡ ይዘቶች ወይም ዱየቶች (duet) ይጠቀሳሉ።

ይህ የሚያመለክተው በቲክቶክ የምንመለከታቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ ድምጾች፣ ዱየቶች እንዲሁም የጽሁፍ ማብራሪያዎች ሁሉ ትክክለኛ መረጃ የያዙ ላይሆኑ እንደሚችሉ ነው።

ስለሆነም በቲክቶክ የምንመለከታቸው ይዘቶች ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ቆም ብለን ማሰብና መመርመር ያስፈልገናል።

የሚከተሉት የጥንቃቄ ነጥቦችም በሀሠተኛና የተዛቡ መረጃው እንዳንጋለጥ ይረዱናል፤

  •  የተንቀሳቃሽ ምስሉን እና የድምጹን ስምረት እንመርምር: በቲክቶክ የምንመለከታቸው ይዘቶች ተንቀሳቃሽ ምስልና ድምጽ ስምረት ከሌለው የተቀናበረ ሊሆን ስለሚችል መጠንቀቅ ይኖርብናል።

ለዚህ ደግሞ ቲክቶክ ትክክለኛውን ወይም መጀመሪያ የተጋራውን ድምጽ Original Sound) ለማመሳከር እንዲረዳ ያስቀመጠው ቁልፍ ይረዳናል።

ትክለኛውን ወይም መጀመሪያ የተጋራውን ድምጽ ለማግኘት ከቲክቶክ አካውንቱ በስተቀኝ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን ቁልፍ መጫን በቂ ነው። ቁልፉ ‘ Original Sound’ ወደሚል ገጽ ያመራናል።

  • ለድየት (duet) አገልግሎት ተጠቅሶ የቀረበውን ይዘት እንፈልግ: በድየት መልክ የቀረበ ይዘት ትክክለኛነቱን ከተጠራጠሩ ወይም ከአውድ ውጭ ተወስዷል ብለው ካሰቡ ለድየት አገልግሎት የተጠቀሰውን ኦሪጅናል ቪዲዮ ወይም ድምጽ ይፈልጉ።

ለዚህም የቲክቶክ ፍለጋ (tiktok search) ወይም የኦሪጂናል ሳውንድ (Original Sound) ቁልፍ ይረዳወታል።

  • የምልሰት መፈለጊያ መተግበሪያዎችን (Reverse image search tools) እንጠቀም: በቲክቶክ የምንመለከታቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከአውድ ውጭ የቀረቡ ወይም የቆዩ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ካሰቡ እንደ ጎግል ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች (Google Reverse Image Search) ፣ ቲንአይ (Tineye)  እና ያንዴክስ (Yandex) በመሳሰሉ የምልሰት መፈለጊያ መተግበሪያዎችን ይጠቀሙ። ይህን ለማድረግም በመጀመሪያ ከቪዲዮው ስክሪን ቅጅ (screenshot) ይውሰዱ፤ በመቀጠልም የወሰዱትን የስክሪን ቅጅ በምልሰት መፈለጊያ መተግበሪያዎች ላይ በማስገባት ይፈልጉ።

በቅንብር ተሰርተው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ከሚቀርቡ ሀሰተኛ የፅሁፍ፣ የምስል፣ የድምፅ እንዲሁም የቪድዮ መረጃዎች ራሳችንን እንጠብቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::