ይህ ምስል በጎንደር የተደረገ የመንገድ መዝጋት ተቃውሞን አያሳይም

image doesn't show protest in Gondar city ይህ ምስል በጎንደር የተደረገ የመንገድ መዝጋት ተቃውሞን አያሳይም

መጋቢት 30፣ 2015

ሸዋ ሚዲያ ሰርቪስ (Shewa Media Service – SMS) የሚል ስያሜ ያለው የፌስቡክ ገጽ በአሁኑ ሰአት በጎንደር ከተማ መንገድ በድንጋይ በመዝጋት ተቃውሞ እየተካሄደ እንደሆነ ለማሳየት “ጎንደር!!” ከሚል ጽሑፍ ጋር ያጋራውን ምስል ተመልክተናል።

ይህ ከ65 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ እንደሆነ የሚገልጹ መልእክቶች እያጋራ ሲሆን በጎንደር ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ይሄንን ምስል ተጠቅሟል።

ሆኖም ከላይ የተጠቀሰው አካውንት ያጋራው ምስል ከአራት አመት በፊት በሱዳን ካርቱም ከተማ ውስጥ ከተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች የተወሰደ መሆኑን ኢትዮጽያ ቼክ በሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች (reverse image search) ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል።

ምስሉ ‘አልታሂር’ (Altaghyeer) የተባለ የሱዳን የኦንላይን ጋዜጣ እ.አ.አ ግንቦት 1/ 2019 ዓ.ም ላይ በካርቱም የተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች አስመልክቶ በሰራው ዘገባ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ሙሉው ሪፖርት ይህንን ማስፈንጠሪያ በመከተል ማግኘት ይቻላል: ሊንክ

ሰሞኑን የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ያሉ ልዩ ሀይሎችን በፌደራል የጸጥታ መዋቅሮች እና በመከላከያ ሀይል ውስጥ የማካተት ስራ መንግስት መጀመሩን ተከትሎ ይህንን በተቃወሙ አካባቢዎች ውጥረት መኖሩ ተዘግቧል።

የአማራ ክልል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ተግባር በሁሉም ክልሎች የሚከናወን መሆኑን በመጥቀስ “የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው” ብሏል።

ይሁንና ይህን የመንግስት እርምጃ የሚቃወሙ ድምፅች መሰማት የጀመሩ ሲሆን እንደ አብን ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተቃውመውት መግለጫ አውጥተዋል፣ በአንዳንድ ስፍራዎችም መንገድ የመዝጋት እንቅስቃሴዎች እንደተስተዋሉ ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው የሚድያ ቅኝት ማየት ችሏል።

በቅንብር ከሚሰሩ እና ከአውድ ውጭ ከሚቀርቡ አሳሳች ምስሎች፣ ቪድዮዎች እና ጽሑፎች ራሳችንን በመጠበቅ የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::