ይህ ምስል ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ደስታቸውን ለመግለፅ አደባባይ የወጡ የሶማሊላንድ ነዋሪዎችን አያሳይም

ይህ ምስል ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ የሶማሊላንድ ነዋሪዎችን አያሳይም

ታህሳስ 25፣ 2016

በያዝነው ሳምንት መጀምሪያ ኢትዮጵያ ለወታደራዊ እና ለባሕር ንግድ አገልግሎት የሚውል የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ  ጋር መፈራረሟን አስታውቃለች።

የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ “ለሪፐብሊክ ኦፍ ሶማሊላንድ” በይፋ እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሀገር እንደምትሆን ተናግረዋል።

ይህን የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መግባቢያ ሰነድ መፈራረም ተከትሎም የተለያዩ መረጃዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲጋሩ ሰንብተዋል። ከነዚህ መካከልም የሶማሊላንድ ነዋሪዎች በስምምነቱ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹ ያሳያሉ የተባሉ ምስሎች ይገኙበታል።

‘KIYYA Hararghe’ የሚል ስምና ከ380 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽም ስክሪን ቅጂው የሚታየውን ምስል “የሶማሊላንድ ህዝብ በአደባባይ ወጥቶ ደስታዉን ሲገልፅ አድሯል” ከሚል ጽሁፍ ጋር አጋርቷል።

በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም መረጃውን መልሰው አጋርተውታል፤ በርካቶችም ሀሳብና አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ምስሉ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የፈረመችውን የመግባቢያ ሰነድ በማስመልከት ደስታቸውን ለመግለጽ የወጡ የሶማሊላንድ ሰልፈኞችን አያሳይም።

ይህ ምስል ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜዎች በፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር ከነበረ ቪድዮ የተወሰደ ስክሪን ቅጂ (screenshot) ነው።

ምስሉ የተወሰደበትን ቪድዮ ካጋሩ የፌስቡክ አካውንቶች መካከልም ‘Siciid Yuusuf Aar’ የሚል ስም ያለው አካውንት አንዱ ሲሆን ቪድዮውንም አኤአ ግንቦት 17 2022 ነበር ያጋራው።

‘KIYYA Hararghe’ በሚል ስም የፌስቡክ ገጽ የተጋራው ምስልም በዚህ ቪድዮ 0፡03 ሴኮንድ ላይ ይገኛል፡ https://www.facebook.com/share/v/pN3ivrxeMzLXQARx/?mibextid=KMUjF5

ስለዚህም ይህ ምስል ከአውድ ውጭ የተጋራና አሳሳች ሆኖ አግኝተነዋል።

ጊዜያቸውን ባልጠበቀና ከአውድ ውጭ በሆነ መልኩ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ጥንቃቄና ማጣራት እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::