የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚገኝ የስራ አጦች ቁጥር መጨመር ለጨፌ ያቀረቡት የተሳሳተ መረጃ
ሐምሌ 05፣ 2015
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ከገጠሙ ችግሮች መካከል አንዱ ስራአጥነት መሆኑን ከትላንት በስቲያ ሐምሌ 03/2015 ከጨፌ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ጠቅሰው ነበር።
ችግሩ በተለያዩ የዓለም ሀገራትም ፈተና መሆኑን የተናገሩት ፕሬዘዳንቱ የስራ አጦች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃከ16% በላይ ማደጉን ተናግረዋል።
ይህ ንግግራቸዉም በዚህ የኦ ቢ ኤን ቀጥታ ስርጭት ማስፈንጠሪያ ከ2:36:45 ጀምሮ ይገኛል፡ https://fb.watch/lJqqMYbnKz/?mibextid=v7YzmG
በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ዉስጥ ያለዉን የስራ አጥነት ችግር በማንሳት “በደቡብ አፍሪካ የስራ አጦች ቁጥር በ60% አድጓል፣ በናይጄሪያ ብቻ በ53% አድጓል” ብለዋል። በተመሳሳይ በቻይናም የስራ አጦች ቁጥር በ20% ማደጉን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬዘዳንቱ ያቀረቧቸው መረጃዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በጉዳዩ ተአማኒ መረጃዎችን በማቅረብ ከሚታወቁ ተቋማት መረጃ ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነ ተመልክተናል።
የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው ዓለም አቀፍ የስራ አጦች ብዛት በ2019 5.5% ነበር። በ2020 6̈.9%፤ በ2021 6.2% እና በ2022 5.8% እንደሆነ ያሳያል: https://data.worldbank.org/indicator/SL.UEM.TOTL.ZS
የዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት ILO የ2023 ግምትም 5.8% ነው፡ https://ilostat.ilo.org/data/#
በዚሁ መሰረት የሁለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የስራ አጦች ቁጥር ከ16% በላይ ማደጉን የሁለቱ ተቋማት መረጃዎች አያሳዩም።
የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት IMF መረጃ እንደሚያሳየው በ2020 በደቡብ አፍሪካ የነበረው የስራ አጦች ቁጥር29.2% ሲሆን በ2021 ወደ 34.3% ከፍ ብሎ ነበር።
በ2022 ደግሞ 33.5% የነበረ ሲሆን የ2023 ግምትም 34.7% ነው፡https://www.imf.org/external/datamapper/LUR@WEO/WEOWORLD/ZAF
ይህ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት መረጃም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት በሀገሪቱ የስራ አጦች ቁጥር በ60% ማደጉን ወይም መጨመሩን አያሳይም።
በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፉት ሶስት ዓመታት የቻይና የስራ አጥ ዜጎች ምጣኔ ከፍተኛው 4.2 % ሲሆን ዝቅተኛውደግሞ 4% ነው።
ይህም የቻይና የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር በፕሬዘዳንቱ በተገለጸው ደረጃ በ20% እንደተጠቀሰው ያለማደጉን የሚያመላክት ነው፡https://www.imf.org/external/datamapper/LUR@WEO/OEMDC/ADVEC/WEOWORLD/CHN
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::