“ለህወሃት የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ተሰጠ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሀሠተኛ ነው”- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ቼክ

the-national-election-board-of-ethiopia-said-the-certification-of-tplf-is-fake

ጥር 23፣ 2016 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠቱን ያሳያል የተባለ ሰርተፊኬት በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ሲሰራጭ ተመልክተናል።

ሰርተፊኬቱ በ22/05/2016 ዓ.ም ስለመሰጠቱም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ቼክ ከላይ የተገለጸውን የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ቦርዱን አነጋግሯል።

ከቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ሥራ ክፍል ባገኘነው መረጃ መሠረት የተጋራው መረጃ ሀሠተኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ሰርተፊኬቱም ተመሳስሎ የተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በሚሰጥበት ወቅት በኦፊሴላዊው የፌስቡክ ገጹ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።

ምርጫ ቦርዱ ‘የወሎ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ’ ተብሎ ለሚጠራ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ፤ ‘የኩሽ ህዝቦች ብሔራዊ ንቅናቄ’ ተብሎ ለሚጠራ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ እና ‘ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ’ ለተባለ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ጥር 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ይፋ አድርጎ ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ለህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ተሰጥቶት የነበረው የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መሰረዙ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::