የሆሎግራም ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ግዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰራ በሚል የቀረበው መረጃ የተሳሳተ ነው

The information provided by PM Abiy about hologram technology being developed in Ethiopia for the first time in Africa is incorrect.

የካቲት 5፣ 2016 ዓ.ም

ባሳለፍነው እሁድ የአድዋ ድል የመታሰቢያ ሙዚየም በተመረቀበት አለት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በባለ ሶስት አውታር ሆሎግራም (3D Hologram) ቴክኖሎጂ አማካኝነት ከታዳሚዎች ፊት ቀርበው ንግግር ማድረጋቸው ተመልክተናል።

ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ መድረኩ ላይ በሆሎግራም አማካኝነት ከመከሰታቸው ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቴክኖሎጂውን በተመለከተ ንግግር አድርገው ነበር።

በንግግራቸውም “የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ለመጀመሪያ፤ በዓለም እጅግ ጥቂት ሀገራት ሊያሳኩ የቻሉትን የሆሎግራም ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ሦስት ፎቶ እና ባልጠራ ድምጽ የተቀዳ የአፄ ምኒሊክ ንግግርን በአዲስ መልዕክት እና በዛሬ ምንነት አስደማሚ በሆነ መልኩ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመቶ ዓመት በፊት የሞቱትን ሰው ሊያናግር ጥቂት ደቂቃዎች ቀርተውታል፡፡ ትላንት አባቶቻችን ቴክኖሎጂን ሞክረዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነውን ምልክት ሊያሳየን ተዘጋጅቷል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆሎግራም ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለዕይታ መቅረቡን በተመለከተ የተናገሩት መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት አረጋግጧል።

የባለሶስት አውታር ሆሎግራም ቴክኖሎጂ ባለፉት ጥቂት አመታት በግብጽ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በታንዛኒያ እና በናይጄሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ተመልክተናል።

ግብጽ ከሁለት አመት በፊት አራተኛውን የአለም ወጣቶች ፎረም ባዘጋጀችበት ወቅት የፊዚክስ ሊቁን አልበርት አንስታይን፣ ታላቁን ባለቅኔ ጃላል አል-ዲን አል-ሩሚን እና ማዘር ትሬሳን የባለ ሶስት አውታር ሆሎግራም በመጠቀም ለእይታ አብቅታ ነበር። በዝግጅቱ ላይም የሀገሪቱ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ተገኝተው ነበር። ዝርዝሩን ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ያግኙ: https://www.egypttoday.com/Article/4/112091/Aroma-Studios-takes-hologram-technology-to-a-whole-new-level

በታንዛኒያ ደግሞ ቮዳኮም የተሰኘው የቴሌኮም ኩባንያ ከአመት በፊት የ5ኛ ትውልድ አገልግሎቱን ይፋ ባደረገበት ስነ-ስርዐት የባለ ሶስት አውታር ሆሎግራም ተጠቅሞ ነበር። ቴክኖሎጂውን ያቀረበውም መቀመጫውን ናይሮቢ፣ ኬኒያ ያደረገው ጄይስ ፓይሮቴክኒክስ (Jays Pyrotechnics) የተባለ ኩባንያ ነበር። የሆሎግራሙን እይታ ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ይመልከቱ: https://www.youtube.com/watch?v=seDPEeNMl5M

በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱትን አገሮች ጨምሮ ቴክኖሎጂው ለማስታወቂያ፣ ለትምህርት፣ ለሽያጭ ስራ (marketing) እና ለሌሎችም አገልግሎት በመዋል ላይ መሆኑን ተመልክተናል።

ሆሎግራም እ.አ.አ 1948 ዓ.ም በሀንጋሪያዊው ዴቪስ ጋቦር የተፈጠረ ሲሆን በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ እጅጉን እየዘመነ በመሄድ ላይ የሚገኝ ቴክኖሎጂ መሆኑ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::