አል አይን አማርኛ በአፍሪካ ስለሚገኙ አየር መንገዶች እና አውሮፕላኖች ቁጥር ያቀረበው አሳሳች መረጃ

መጋቢት 18፣ 2016 ዓ.ም

አል አይን አማርኛ በትናንትናው እለት ‘በርካታ አውሮፕላኖች ያሏቸውን ሀገራት ዝርዝር’ በማለት አንድ መረጃ አጋርቶ ነበር፣ ለዚህም የፕሌን ስፖተርስ ድረ-ገጽ መረጃን መሰረት አድርጓል።

በዚህ መረጃ መሰረት ደቡብ አፍሪካ በ195 አውሮፕላኖች አንደኛ፣ ኬንያ በ177 አውሮፕላኖች ሁለተኛ፣ ግብፅ በ166 አውሮፕላኖች ሶስተኛ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በ142 አውሮፕላኖች አራተኛ ደረጃን እንደያዙ ዘገባው ይጠቁማል (ስክሪን ቅጂው ተያይዟል)።

ይህ የአል አልይን ዘገባ በመግቢያው በአፍሪካ ስለሚገኙ አየር መንገዶች ሀተታ ስላቀረበ ያቀረበው ቁጥርም ስለነዚህ አየር መንገዶች እንደሆነ ያመላክታል።

ይሁንና በአቪዬሽን ዘርፍ በሚሰራቸው ዘገባዎች የሚታወቀው ሲምፕል ፍላይንግ (Simple Flying) የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ባወጣው ሪፖርት በአፍሪካ ከሚገኙ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ133 አውሮፕላኖች ቀዳሚው፣ የግብፅ አየር መንገድ በ82 አውሮፕላኖች ሁለተኛ፣ የአልጄርያ አየር መንገድ በ55 አውሮፕላኖች ሶስተኛ፣ የሞሮኮ አየር መንገድ በ51 አውሮፕላኖች አራተኛ እንዲሁም የኬንያ አየር መንገድ በ32 አውሮፕላኖች አምስተኛ እንደሆነ ዘግቧል ( https://simpleflying.com/largest-airlines-africa/  )

ይህን የሚያረጋግጠው ሌላው መረጃ ለምሳሌ የግብፅ አየር መንገድ በራሱ ድረ-ገፅ የአውሮፕላኖቹ ቁጥር 80 ገደማ እንደሆነ አስቀምጧል። በኪሳራ ላይ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ ደግሞ አሁን ላይ ያሉት አውሮፕላኖች 13 ብቻ እንደሆኑ በድረ-ገፁ ላይ ይታያል።

የአል አይን ዘገባ በአጠቃላይ በተጠቀሱት ሀገራት ውስጥ ስለሚገኙ አውሮፕላኖች ቢሆን ምናልባት ትክክል ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙን አንድ የአቪዬሽን ባለሙያ፣ እንደ ኢትዮጵያ አንድ ግዙፍ አየር መንገድ እና ጥቂት የግል የቻርተር በረራ የሚሰጡ ድርጅቶች ሳይሆኑ በርካታ የግል አየር መንገዶች እና የግል አውሮፕላኖች ያሉባቸው ሀገራት እንዳሉ ጠቁመዋል። ስለዚህ ብዙ አውሮፕላኖች ያሏቸው ሳይሆን ያሉባቸው ሀገራት ተብሎ መቅረብ እንደነበረበት ባለሙያው አስረድተዋል።

ይሁንና የዜናው ቅኝት በአየር መንገዶች ዙርያ ስለሆነ መረጃውን አሳሳች ያደርገዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::