‘የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቴሌግራም ቻነሉ አማካኝነት ለኢትዮጵያውያን ድጋፍ እየሰጠ ነው’ በሚል እየተሰራጨ ከሚገኝ ሀሰተኛ መረጃ እንጠንቀቅ!

'የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቴሌግራም ቻነሉ አማካኝነት ለኢትዮጵያውያን ድጋፍ እየሰጠ ነው' በሚል እየተሰራጨ ከሚገኝ ሀሰተኛ መረጃ እንጠንቀቅ!

መስከረም 23፣ 2016

ከሰሞኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) በቴሌግራም ቻነሉ አማካኝነት ለኢትዮጵያውያን ድጋፍ እየሰጠ ነው የሚል የጽሁፍ መረጃ በቴሌግራም ሲሰራጭ ተመልክተናል።

ይህ ለቴሌግራም ተጠቃሚዎች እየተላከ የሚገኘው መልዕክት ድጋፍ ማግኘት የሚሹ ሰዎች ከመልዕክቱ ጋር የተጋራውን መዳረሻ (ሊንክ) እንዲጫኑም ይመክራል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ በኢትዮጵያ የተመድ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የልማት ማስተባበሪያ ኦፊሰር የሆኑትን አቶ ጌታቸው ዲባባን መረጃ የጠየቀ ሲሆን እርሳቸዉም መረጃው ሀሰት መሆኑን ነግረዉናል።

“የተባበሩት መንግስታት (UN) ይህን መግለጫ እንዳላወጣና ከተጋራው ሊንክ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ልናሳውቃችሁ እንወዳለን” ብለዋል ኦፊሰሩ።

በተጨማሪም ተቋሙ ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን የሚደርስበት የራሱ አሰራር እንዳለው የገለጹት አቶ ጌታቸው ተመድ “ሰበዓዊና የልማት ድጋፎችን ለማድረግ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ደንበኝነት (subscription) እና ጉብኝት እንደ መስፈርት አይጠቀምም” በማለት አክለዋል።

ህብረተሰቡም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ስም በመጠቀም ከሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል።

ተዓማኒ ባልሆኑ ምንጮች የሚጋሩ አጠራጣሪ ማስፈንጠርያዎች (ሊንኮች) ለመጭበርበር እንዲሁም ስልካችን እና ኮምፒተራችንን ለቫይረስ ጥቃት ሊዳርጉ ስለሚችሉ ከመክፈታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።

አጠራጣሪ ሊንኮችን እንዴት ማጣራት እንደሚቻል ለማወቅ ይህን በኢትዮጵያ ቼክ የተዘጋጀ ቪድዮ ይመልከቱ፡ https://t.me/ethiopiacheck/1707

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::