ቴሌ ብርን በመምሰል በቴሌግራም አማካኝነት እየተፈፀመ የሚገኝ የማጭበርበር ድርጊት

Telebirr Online scam alert

ነሐሴ 10፣ 2015 ዓ.ም

ከሰሞኑ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት የሆነውን ቴሌ ብርን መስሎ በመቅረብ እና የተለያዩ ሰዎችን በማናገር እየተፈፀመ የሚገኝ የማጭበርበር ድርጊት እንዳለ ኢትዮጵያ ቼክ መመልከት ችሏል።

ይህ የቴሌግራም ቻናል ቦት “Telebirr Online customer servive” የሚል ስም ያለው ሲሆን የቴሌ ብር አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ደረጃ ለማሳደግ (upgrade ለማድረግ) በሚል የስልክ እና የሚስጥር ቁጥር በመጠየቅ የሚሰራ የማጭበርበር ድርጊት እንደሆነ ማየት ችለናል።

“የቴሌ ብር ደንበኝነት ደረጃን (customer level) በኦንላይን ለማሳደግ በመጀመርያ ትክክለኛ የእርስዎ አካውንት እና ስልክ ቁጥር መሆኑን ማረጋገጥ ስላለብን ሙሉ ስም፣ ስልክ ቁጥር እና የቴሌ ብር ይለፍ ቃል (PIN CODE) ይላኩልን። በመቀጠል ከጥሪ ማዕከላችን የምንልክሎትን ስድስት ዲጂት የማረጋገጫ ኮድ (verification code) ይልኩልናል፣ ይህን አገልግሎት ለማግኘት ቢያንስ 1 ሺህ ብር አካውንትዎ ላይ ሊኖር ይገባል” በማለት የማጭበርበር ድርጊት እየተፈፀመባቸው እንደሆነ አንዳንድ ግለሰቦች ለኢትዮጵያ ቼክ አሳውቀዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ መገንዘብ እንደቻለው አንድ ሰው ስልክ ቁጥሩን እና የይለፍ ቃሉን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ከሰጠ የማረጋገጫ ቁጥሩ (verification code) እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል። ይህን ከኢትዮ ቴሌኮም የሚመጣ የማረጋገጫ ቁጥር አሳልፎ መስጠት ደግሞ ለዘረፋ ያጋልጣል።

በዚህ ዙርያ ኢትዮጵያ ቼክ ኢትዮ ቴሌኮምን ያነጋገረ ሲሆን የድርጅቱ ዋና የኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ይህ የቴሌግራም ቦት ሀሰተኛ መሆኑን አረጋግጠው “እኛ ብቸኛ የምንጠቀምበት ቦት “አርዲ/Ardi” የሚባል ሲሆን ይህም በተረጋገጠው የቴሌብር አካውንቶች ላይ ይገኛል” ብለዋል።

የማረጋገጫ ቁጥርን አሳልፎ መስጠት ለመጭበርበር ስለሚያጋልጥ ጥንቃቄ እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::