በተባለው ደረጃ (በፀሀይ ጨረር) ምክንያት በሰው ላይ ሊደርስ የሚችል ቀጥተኛ ጉዳት የለም” የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት

መጋቢት 8፣ 2016 ዓ.ም

በርከት ያሉ የፌስቡክ ገጾችና አካውንቶች ከመጋቢት 7-10 ድረስ በአዲስ አበባ በሰው ቆዳ እና ስነ ተዋልዶ ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ከፍተኛ የፀሀይ ጨረር እንደሚኖር መረጃ እያጋሩ ይገኛሉ።

ከነዚህ መካከል 100ሺህ ተከታዮች ያሉት ‘Wasu Mohammed – ዋሱ መሀመድ  Page’ የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ “በአዲስ አበባ ከሚያጋጥመው ከፍተኛ የፀሀይ ጨረር የተነሳ ከቀኑ ከ5:00—10:00 ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ መረጃዎች ያመለክታሉ” ሲል መረጃውን አጋርቷል።

“በጠራራ ሰዓት አንድም በቤት(በሱቅ) ውስጥ መቀመጥ፣ ለእንቅስቃሴ ጥላ መያዝ ይገባል” የሚሉት ደግሞ የባለሙያዎች ምክር እንደሆኑም ተጠቅሷል።

ጉዳዩን በተመለከት ኢትዮጵያ ቼክ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትን ምላሽ የጠየቀ ሲሆን በኢንስቲትዩቱ የኢንስትሩመንቴሽን ቡድን መሪ ተመራማሪ የሆኑት ኢንጂነር ግዮን አሸናፊ እንዲሁም  የስፔስ እና ፕላኔተሪ ሳይንስ መሪ  ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር ንጉሴ መዝገበ ማብራሪያ ሰጥተውናል።

ኤም ክላስ (M- class) የተሰኘው የፀሀይ ነበልባል (solar flare) እንቅስቃሴ መታየቱን የነገሩን ሁለቱ ተመራማሪዎች ይህ እንቅስቃሴ እድገቱ ከቀጠለ አልፎ አልፎ የኮሙኒኬስን መስተጓጎል እና አነስተኛ የአሰሳ ስህተቶች (navigational errors) ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ነገር ግን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተሰራጨ በሚገኘው መረጃ ደረጃ በሰዎች ላይ ጉዳት የሚያመጣ ነገር አንደሌለ ገልጸዋል።

በማህበራዊ ትስስር ገጾች በተገለጸው ደረጃ “በሰዎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ቀጥተኛ ጉዳቶች አይኖሩም” ብለዋል።

“የኛን ሀገር በተመለከተ አፌክት የሚያደርጉን (ጉዳት የሚያደርሱ) የተለዩ ነገሮች የሉም” ያሉት ኢንጂነር ግዮን በዓለም አቀፍ ደረጃም ይህን ጉዳይ በተመለከተ የተተነበየ ነግር እንደሌለም ነግረውናል።

በተጨማሪም “በተለይ እንደ ሀገር ካለንበት የጂኦግራፊ አከባቢ አንጻር የምድር ወገብ አከባቢ እንደመሆናችን (የፀሀይ ነበልባልን) ጉዳት የምናየው ወደ ሰሜን ንፍቀ ክበብ ላይ ያሉ ሀገሮች አከባቢ ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል ከፀሀይ ተቦጭቀው የሚወጡና ወደ ምድር የሚጓዙ የሶላር ቅንጣቶች (particles) መኖራቸውን የተናገሩት ተመራማሪው እነዚህ ቅንጣቶች ቀናታና ሳምንታን በሚፈጅ ጊዜ ወደ ምድር እንደሚደርሱ ይናገራሉ።

“እነዚህ ጨረሮች በብዛት የሚያጠቁት ወይም አደጋ ያደርሳሉ ተብሎ የሚጠበቀው በተለይ ስፔስ ላይ ያሉ የሳተላይት አካላትን/ሳተላይቶችን ነው” ብለዋል።

እነዚህ ቅንጣቶች ሳተላይቶች ላይ ጉዳት ከማድረሳቸዉም በተጨማሪ የመገናኛ መሳሪያዎች እና ኮሙኒኬሽን ላይ ተግዳሮት የመፍጠር እቅም እንዳላቸውም ኢንጂነር ግዮን አሸናፊ ጠቅሰዋል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::