በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ስም እየተፈፀመ ያለ የማጭበርበር ድርጊት

መጋቢት 28፣ 2016 ዓ.ም

ከ180,000 በላይ ተከታይ ያለው አንድ ቬሪፋይድ የሆነ የቴሌግራም ቻናል ፈጣን የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እየሰበሰበ ይገኛል።

በ15 ቀን ፖስፖርት ለማግኘት 4,500 ብር፣ በ10 ቀን 6,800፣ በ5 ቀን 8,000 ብር እና በ2 ቀን 12,000 ብር በግል የንግድ ባንክ አካውንቶች እየሰበሰቡ ይገኛሉ።

እስካሁን ብቻ ለኢትዮጵያ ቼክ በደረሱ ጥቆማዎች ገንዘብ እየተሰበሰቡባቸው ያሉት አካውንቶች “አስረስ” በተባለ ግለሰብ የአካውንት ቁጥር 1000533898908 እንዲሁም ‘ህይወት’ በተባለች ግለሰብ የአካውንት ቁጥር 1000522976303 ናቸው።

እነዚህ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሰራተኛ በመምሰል ግለሰቦችን የሚቀርቡ አጭበርባሪዎች የቴሌግራም አካውንታቸው እውነት እንዲመስል ለቴሌግራም ክፍያ በመፈፀም ቬሪፋይድ አስደርገዋል። ፖስፖርት ለማግኘት በጣም እየተንገላታ ያለውን ህዝብ ታርጌት በማድርግ እየመዘበሩ ይገኛሉ።

በዚህ ዙርያ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፣ መረጃው ግን ከማስረጃው ጋር ቀርቧል። ቢያንስ እነዚህ አካውንቶች የእነሱ እንዳልሆኑ ለህዝብ ሊያሳውቁ፣ በስማቸው ህዝብን የሚዘርፉትን ደግሞ በህግ ሊጠይቁ ይገባል እንላለን።

ትክክለኛው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የቴሌግራም ቻናል 134,000 ገደማ ተከታይ ያለው ይህ ነው: https://t.me/ICS_Ethiopia

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::