ግልጽነት በጎደላቸው የግብይት ማስታወቂያዎች ከመታለላችን በፊት ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ

scam ads

ሰኔ 1፣ 2015 ዓ.ም

የማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በኢንተርኔት አማካኝነት በርካታ ማስታወቂያዎችን እንመለከታለን። የምንመለከታቸው ማስታወቂያዎች ሁሉ ግን ትክክለኛ እና የተሟላ መረጃ የሚሰጡ ላይሆኑ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ግልጽና የተሟላ መረጃ የሚሰጡና ህጋዊና መሆናቸውን በቀላሉ ማጣራት የሚቻሉ ናቸው።

በአንጻሩ አንዳንዶች ህጋዊ የሚመስሉ ግን ግልጽነት የሚጎላቸውና የተሟላ መረጃ የማይሰጡ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ አምታች ማስታወቂያወች ለመጭበርበር በር የሚከፍቱና ጸጸት እና ኪሳራ ላይ ሊጥሉ ስለሚችሉ ከማመናችንና ግብይት ከመፈጸማችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል።

በማስታወቂያው የተጠቀሱ መረጃዎችን ማጣራት:
የግብይት ማስታወቂያዎችን ከማመናችንና ግብይት ከመፈጸማችን በፊት በማስታወቂያው የተጠቀሱ መረጃዎች ግልጽ፣ የተሟሉና ህጋዊ መሆናቸውን ማጣራት ጠቃሚ ነው። ከመረጃዎቹ መካከል ማስታወቂያውን ያስነገረው ድርጅት ህጋዊ መሆኑን ከሚመለከተው የመንግስት ተቋማ ማጣራት ከመታለል ይታደጋል። እንዲሁም ከድርጅቱ ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ማንነት፣ የኋላ መሰረት መመርመር አስፈላጊ ነው። የድርጅቱን አድራሻ፣ የፋይናንስና የባለሙያ አቅም ማጣራትም ጠቃሚ ይሆናል።

ቅናሾችና እና የጊዜ ገደቦችን ይጠንቀቁ:
በግብይት ማስታወቂያው ቅናሽ እና የጊዜ ገደቦች በሚያማልል መልኩ የቀረቡ ከሆኑና ትኩረትዎን ከሳቡ ቆም ብለው ያስቡ። ለግብይት በቅናሽና በጊዜ ገደብ የቀረበውን ነገር ከመደበኛው ገበያ ጋር ያነጻጽሩ። ለምሳሌ በቅናሽና በጊዜ ገደብ የቀረበው የመኖሪያ አፓርታማ ከሆነ ህጋዊ የሪል እስቴት ኤጀንቶችን ማማከር ጥሩ ይሆናል።

ቅድሚያ ክፍያዎችን ከመፈጽም በፊት ባለሙያ ያማክሩ:
የግብይት ማስታወቂያው ቅድሚያ ክፍያዎችን ቶሎ እንዲፈጽሙ የሚጎተጉት ከሆነ ክፍያዎችን ከመፈጸምዎ በፊት የህግ ባለሙያ ያማክሩ። ይህም አነስ ባለ ወጭ ከትልቅ ኪሳራ ሊታደግዎ ይችላል።

ግልጽነት የጎደለው እና የተሟላ መረጃ የማይሰጥ ከሆነ ቆም ይበሉ:
የግብይት ማስታወቂያው ግልጽነት የጎደለው እና የተሟላ መረጃ የማይሰጥ ከሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ጥሩ ይሆናል። ማስታወቂያ ወደ አስነገረው ድርጅት በማምራት ተጨማሪ ማብራሪያ መጠየቅም ጠቃሚ ነው። ግብይት ከመፈጸምዎ በፊት የህግ ባለሙያ ማማከርም ተገቢ ይሆናል።

አጠራሪ ነገሮችን ያስተውሉ:
የግብይት ማስታወቂያ ያስነገረው ድርጅት ተጨማሪ መረጃና ማብራሪያ ለመስጠት የሚያንገራግርና ወደኃላ የሚል ከሆነ አልያም የሚያምታታ ከሆነ ይጠንቀቁ። ለተገቢው የመንግስት ተቋምም ሪፖርት ያድርጉ።

እንዲሁም ፕላትፎርማቸው ለማስታወቂያ ማስነግሪያነት የሚከራዩ የሚዲያ ተቋማት ማስታወቂያውን ከማጋራታቸው በፊት ቆም ብለው ማስተዋል ይጠበቅባቸውል። ማስታወቂያ ስለሚያስነግረው ድርጅት ህጋዊነት እና ለማስታወቂያው ግልጽነት ተገቢውን ማጣራት የማድረግ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል። በዚህም ዜጎችን ከመታለልና ከኪሳራ ተቋማቸውንም ከተጠያቂነት ሊያድኑ ይችላሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::