ከሰሞኑ ብቅ ያለው “ABN” የተባለው ማጭበርበርያ መንገድ

ABN scam

ሰኔ 18፣ 2015 ዓ.ም

ABN International የተባለ አካል ወይም ግለሰብ ድረ-ገፁን፣ በዋትሳፕ እንዲሁም ቴሌግራምን በመጠቀም የማጭበርበር ድርጊት እየፈፀመ እንደሆነ ኢትዮጵያ ቼክ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።

የማጭበርበር ድርጊቱ እንዲህ ይከናወናል:

– በመጀመርያ ለሰዎች የ WhatsApp ሊንክ ይልካሉ፣ በመልዕክታቸውም ሰዎችን እየመለመሉ እንደሆነ እና ክፍት የስራ ቦታ እንዳላቸው ያሳውቃሉ፣

– ለዋትሳፕ የሚጠቀሙበት ቁጥር https://wa.me/251975986440 ሲሆን ለስልክ ደግሞ +251910092892 ነው፣

– አንዳንድ ጥያቄዎችን ከጠየቁ በኋላ ሌላ ሊንክ ልከው ድረ-ገፅ ያስተዋውቃሉ፣ ከዛም ለማመን በሚቸግር መልኩ የድረ-ገፁን ሶስት ስክሪን ቅጂ (screenshot) ላኩልን ብለው 80 ብር ይከፍላሉ። ደጋግመው ይህን በማድረግ የተጠቃሚውን እምነት (trust) ለማግኘት ጥረት ያረጋሉ፣ “እነዚህማ በትክክል ይከፍላሉ” እንዲባሉ ያደርጋሉ፣

– ቀጥሎም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንት ልከው “40 ብር ካስገባህ 80 ብር፣ 1 ሺህ ብር ካስገባህ 2 ሺህ እንልካለን” ብለው ቃል ይገባሉ፣

– ለትንንሽ ብሮች ቃል በገቡት መሰረት መልሰው በእጥፍ ይከፍላሉ፣ ከዛም ቀስ ብለው እስከ 10 ሺህ፣ 50 ሺህ ወይም 100 ሺህ ሲላክላቸው ግን ገንዘቡን ይዘው ይሰወራሉ።

ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ተከታታይ ማጣራት እነዚህ ግለሰቦች ወይም አካላት ገንዘብ የሚቀበሉባቸው እና ይህን ድርጊት የሚፈፅሙባቸው የባንክ አካውንቶች ስሞች “Chosen Generation” እና “Yenege Tesfa” ናቸው።

በአቋራጭ እና ካለስራ ገንዘብ እናስገኛለን ከሚሉ አካላት በመራቅ ራሳችንን ከመጭበርበር እንከላከል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::