የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት በሆነው M-PESA ስም እየተሰራጩ ከሚገኙ የማጭበርበሪያ መረጃዎች እንጠንቀቅ!

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎት በሆነው M-PESA ስም እየተሰራጩ ከሚገኙ የማጭበርበሪያ መረጃዎች እንጠንቀቅ!

ሐምሌ 05፣ 2015

‘Mpesa Ethiopia’ የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገጽ ሀሰተኛ እና የማጭበርበሪያ መረጃዎችን እያጋራ መሆኑን ተመልክተናል።

ይህ ከተከፈተ አንድ ወር ገደማ የሆነው ገጽ ‘MPESA 1 አመት የሚከፈል እስከ 50,000 ብር የብድር አገልግሎት ለደንበኞቹ አመቻችቷል! እድሉን ይጠቀሙየሚል መረጃን በተደጋጋሚ እያጋራ ይገኛል።

መመዝገብ የሚፈልጉም ሙሉ ስማቸዉን እስከ አያት እንዲሁም ስልክ ቁጥራቸዉን በመልዕክት ማስቀመጫ (inbox) ወደ ገጹ እንዲልኩ ይመክራል።

እስካሁን 2000 ሰዎች በላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚገልጸው ሀሰተኛ መረጃም በተለያዩ የፌስቡክ ግሩፖች ላይ እየተጋራ እንደሚገኝም ተመልክተናል።

ይህን መረጃ በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ማናጅር የሆኑትን ተወዳጅ እሸቱን ያናገረ ሲሆን መረጃው ሀሰት መሆኑን ነግረውናል።

M-PESA “አገልግሎት ኦፊሺያሊ አልጀመርንምሲሉም የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ማናጅሯ ተናግረዋል።

በተጨማሪም M-PESA አገልግሎት ራሱን የቻል ወይም የተለየ የፌስቡክ ገጽ እንደሌለው የገለጹ ሲሆን የተቋሙ መረጃዎች በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ትክክለኛ ፌስቡክ ገጽ ላይ የሚጋሩ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ትክክለኛ ፌስቡክ ገጽ በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል፡https://www.facebook.com/SafaricomET

በሌላ በኩል ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ M-PESA የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፊያ እና መገበያያን ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱ ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::