ዜጎች ያልተገደበ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ለሀሠተኛ መረጃ የመጋለጥ እድላቸው ይቀንሳል

access to unlimited information reduces the risk of being exposed to false and distorted information

የካቲት 27፣ 2015 ዓ.ም

ዜጎች ያልተገደበ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ለሀሠተኛ መረጃ የመጋለጥ እድላቸው ይቀንሳል?

መረጃ መሻት፣ ማግኘትና ማካፋል የሰው ልጆች ሁሉ መሰረታዊ መብት ነው። ይህም እአአ በ1948 ዓ.ም በፀደቀው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 19 በግልጽ ተቀምጧል።

የኢፌድሪ ህገ-መንግስትም በአንቀጽ 29 ይህን መሰረታዊ መብት አጽንቶታል።

ይህ መብት ዜጎች ትክክለኛና የተሟላ መረጃ በወቅቱ እንዲያገኙ በማስቻል በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ያስችላል።

እንዲሁም ዜጎች በማህበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የነቃና አዎንታዊ አስተዋጾ እንዲያበርክቱ ይረዳል።

በተጨማሪም ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖሩ በማድረግ የተረጋጋና ሰላማዊ ምህዳር እንዲኖር ያስችላል።

በአንጻሩ የዜጎች መረጃ የመሻት፣ የማግኘት እና የመስጠት መብት ሲታቀብ ክፍተቱ ለሀሰተኛ መረጃ ያጋልጣቸዋል።

እንዲሁም በተዛባ መረጃ፣ በሴራ ትንታኔ እንዲሁም በአሉባልታ የመሞላት እድሉ ከፍ ይልና ስሜታዊነት፣ አለመተማመን፣ አለመረጋጋት እንዲሁም ግጭት ይሰፍናል።

ይህ መሰረታዊ መብት የሚረጋገጠው ጋዜጠኞችን ጨምሮ መረጃ የሚሹ ዜጎች ወቅቱን የጠበቀ፣ ትክክለኛና የተሟላ መረጃ የሚያገኙበትን እድል በማመቻቸት ነው።

ይህ መሰረታዊ መብት የሚረጋገጠው ጠንካራ፣ ነጻና ገለልተኛ ሚዲያዎች እንዲኖሩ በመደገፍና በማበረታታት ነው።

ይህ መሰረታዊ መብት የሚረጋገጠው መረጃ የመስጠት ግዴታ ያለባቸው አካላት ለመረጃ ጠያቂዎች ያለገደብና አድሎ በራቸውን ክፍት ሲያደርጉ ነው።

ይህ መሰረታዊ መብት የሚረጋገጠው የኢንተርኔትና የዲጅታል መገናኛ ዘዴዎች ጨምሮ በሌሎች የመረጃ መለዋወጫ አውታሮች ከመስተጓጎልና ከዕቀባ ነጻ ሲሆኑ ነው።

ይህ መሰረታዊ መብት የሚረጋገጠው ግጭትና አለመረጋጋት የሚሰተዋልባቸው አካባቢዎች ጋዜጠኞችን ጨምሮ መረጃ ለሚሹ አካላት በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ ሲሆኑ ነው።

ይህ መሰረታዊ መብት የሚረጋገጠው የአደባባይ ሙግቶች፣ ክርክሮችና ውይይቶች ሲበረታቱና ሲደገፉ ነው።

ይህ ከሆነ ዜጎች ወቅቱን የጠበቀ፣ ትክክለኛና የተሟላ መረጃ የሚያገኙ ሲሆን ለሀሠተኛና ለተዛባ መረጃ፣ ለሴራ ትንታኔ እንዲሁም ለአሉባልታ የመጋለጥ እድላቸው ይቀንሳል። ይህም በእወቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ የሚወስን ንቁ ዜጋ እንዲኖር በማስቻል ጠንካራና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር ያስችላል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::