የፈጣን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ከሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች እንጠንቀቅ!

Private messaging apps and the growing risk of scams

ሰኔ 24፣ 2015

እንደ ቴሌግራም፤ ፌስቡክ ሚሴንጀር እና ዋትሳፕ ያሉ ፈጣን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የሚፈጸም የማጭበርበር ድርጊት እየተበራከተ መምጣቱ ይነገራል።

የፈጣን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ከመደበኛው የአጭር መልዕክት አገልግሎት በተለየ መልኩ የሰዎችን የመረጃ ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር (encryption) እንዲሁም ከየትኛዉም የአለም ጫፍ የጽሁፍ፤ድምጽ፤ ምስል እና ቪዲዮ መልዕክቶችን በቀላሉ ለመለዋወጥ አመቺ ሁኔታን ፈጥረዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ መተግበሪያዎች ሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎችን ለማሰራጨት እንዲሁም የተለያዩ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመፈጸም ጥቅም ላይ ሲውሉም ይስተዋላል።

ከነዚህ የማጭበርበር ድርጊቶች መካከልም የተለያዩ ማስፈንጠሪያዎችን (links) በመላክ እነሱን ስንጫን ግላዊ መረጃዎቻችንን መመንተፍ እንዲሁም በታዋቂ ተቋማት ስም ሀሰተኛ የሽልማት መርሀግብሮችን ማስተዋወቅና ለሽልማት ቅድመ ክፍያ በመጠየቅ ማጭበርበር ይገኙበታል።

የፈጣን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ከሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ምካከል አንድ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታይ ላይ ከሰሞኑ የተፈጸመዉን እናጋራችሁ።

ተከታያችን የማጭበርበር ድርጊቱ ሀገረ አሜሪካ በምትገኝ አንድ ጓደኛዉ የፌስቡክ ሚሴንጀር አማካኝነት እንደተፈጸመበት ነግሮናል። 

ይህም አጭበርባሪዎቹ በቅድሚያ ሀገረ አሜሪካ በምትገኘዉን ጓደኛዉን የፌስቡክ አካዉንት ሀክ ያደርጋሉ።

በመቀጠልም ሀክ ያደረጉትን የፌስቡክ ሚሴንጀር መተግበሪያ በመጠቀም ወደ እርሱ መልዕክት ይጽፋሉ። ይህ መልዕክትም ኢትዮጵያ ያለ ዘመድ ድንገት በመቸገሩ እሱ ገንዘቡን እንዲልክለት እና እሷ በነጋታው ጨምራ እንደምትልክለት ይናገራል።

እንዲልክ የተጠየቀዉ የገንዘብ መጠንም 5000 እስከ 7000 ብር ነው።

ተበዳይም በተባለው መልኩ ገንዘቡን ከሀገራችን ባንኮች በአንዱ ወላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ ወደተከፈተ አካውንት ገቢ ያደርጋል።

ይሁን እንጂ በኋላ ላይ የጓደኛው የፌስቡክ አካዉንት ሀክ መደረጉን እና ገንዘብ እንዲልክለት የተጠየቀውም አሜሪካ በምትገኘው ጓደኛው ሳይሆን አካዉንቷን ሀክ ባደረጉ አጭበርባሪዎች መሆኑን ይረዳል።

ተከታያችን በዚህ መልኩ በአጭበርባሪዎች የተወሰደበት ገንዘብ ወጪ እንዳይሆን በባንኩ እንዲታገድ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም አለመሳካቱን ነግሮናል።

ገንዘቡም ኤም እና ሌላ ገንዘብ ወጪ ማድረጊያ አማራጮችን በመጠቀም በፍጥነት ወጪ መደረጉን ባደረገው ክትትል መረዳት እንደቻለም ለኢትዮጵያ ቼክ ነግሯል።

ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ እንዳይጭበረበሩ ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

እኛም የማህበራዊ ትስስር አካዉንቶችና ገጾቻችንን ደህንነት በመጠበቅ እራሳችንን እና ጓደኛ/ወዳጆቻችንን ከአጭበርባሪዎች እንጠብቅ እንዲሁም የፈጣን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ለሚቀርቡን የገንዘብ እና ግላዊ መረጃዎች ጥያቄ አሳልፈን ከመስጠታችን በፊት አስፈላጊዉን ማጣራት እናጥንቃቄ እናድርግ እንላለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::