ከሚከተለው ዝርዝር ውስጥ በአንፃራዊነት ሀሰተኛ መረጃን ከፍ ባለ መጠን ሲያሰራጭ የትኛውን ታዝበዋል/ተመልክተዋል?

poll

ታህሳስ 01፣ 2016 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ቼክ በትናንትናው እለት “ከሚከተለው ዝርዝር ውስጥ በአንፃራዊነት ሀሰተኛ መረጃን ከፍ ባለ መጠን ሲያሰራጭ የትኛውን ታዝበዋል/ተመልክተዋል?” የሚል ጥያቄን ለቴሌግራም ተከታታዮቹ አቅርቦ ነበር።

በተሰጠው መልስ መሰረት መንግስት/የመንግስት አካላት 47%፣ አክቲቪስቶች 32%፣ መላው የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ 11%፣ የተቃዋሚ/አማራጭ ፓርቲ አካላት 5%፣ ሚድያዎች/ጋዜጠኞች 3% እንዲሁም 2% የሚሆኑት መልስ አልተሰጠም ብለዋል።

በአጠቃላይ 975 ሰዎች ድምፅ በመስጠት የተካፈሉበት ይህ የህዝብ መጠይቅ የሀሰተኛ መረጃ ምንጮች እነማን እንደሆኑ ህዝቡ እንደሚያምን ወይም እንደሚገምት ያመላክታል።

ታድያ ይህ የመንግስት አካላት፣ አክቲቪስቶች እና የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ከ1- 3 ያለውን ደረጃ የያዙበት ውጤት ምን ይነግረናል?

ይህ በህብረተሰቡ ዘንድ በሀሰተኛ መረጃዎች ምንጮች ዙርያ ያለውን አስተሳሰብ በወፍ-ዘለል ያመላከተ ሲሆን የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ለሚሰራው ስራም የትኩረት አቅጣጫ በጨረፍታ ያመላከተ ነው። እኛም ይህንን ጉዳይ በአጭሩ እንዳስሰው።

የመንግስት አካላት!

የመንግስት አካላት ሀገርን ከማስተዳደር በተጨማሪ ተገቢ መረጃዎችን በወቅቱ ለህዝብ ማድረስ ሀላፊነታቸውም፣ ግዴታቸውም ነው። ልክ እንደ አክቲቪስቶች ሁሉ በደፈናው መናገር ባይቻልም የመንግስት አካላት የሀሰተኛ መረጃ ምንጮች እየሆኑ እየመጡ እንደሆነ ይታያል። ይህ አደገኛ አዝማሚያ ሲሆን የሀሰት መረጃዎች ቀስ በቀስ ሲጋለጡ እና እውነታው ሲወጣ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው እምነት እንዲቀንስ፣ ብሎም እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመቀነስ ህግ ያወጣ አካል መልሶ ህጉን ሲጥሰው ማየትም አደገኛ አካሄድ (precedent) ያስከትላል። 47 ፐርሰንት የሚሆኑ ድምፅ ሰጪዎች የመንግስት አካላት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ እንዳሉ የሚያመላክት ድምፅ ሰጥተዋል።

አክቲቪስቶች!

በአለም ዙርያ በአክቲቪዝም ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች ስራቸውን ለማከናወን የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ። ከነዚህም መሀል የማህበራዊ ሚድያ ዘመቻዎችን ማስተባበር፣ ሰላማዊ ሰልፎችን ማካሄድ፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በተገኘው አጋጣሚ መሞገት እንዲሁም ስልቶችን ነድፎ ተባባሪዎቻቸውን ለስራ ማነሳሳት ይገኙበታል። እንዳለመታደል ሆኖ በሀገራችን የአክቲቪዝም ስራ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተተወ ይመስል በሌሎች መስኮች ብዙም ሲተገበር አይታይም። ሁሉም ባይባሉም በፖለቲካው ላይ የሚሳተፉት አክቲቪስቶችም የሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት፣ በተራ ስድድብ እና ንትርክ ግዜ በመፍጀት እና የተቃራኒ ሀሳብ ያላቸውን በመዝለፍ እና ስም በማጠልሸት ላይ ተጠምደው ይታያሉ። ይህ ጉዳይ በጣም ግልፅ እየሆኑ ከመምጣቱ አንፃር 32 ፐርሰንት ድምፅ ሰጪዎች አክቲቪስቶች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ እንዳሉ የሚያመላክት ድምፅ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ቼክ ከሁለት አመት በፊት ተመሳሳይ የህዝብ መጠይቅ አድርጎ በውጤቱም 77 ፐርሰንቱ አክቲቪስቶች፣ 42 ፐርሰንቱ የመንግስት አካላት፣ 41 ፐርሰንቱ የተቃዋሚ አካላት፣ እንዲሁም 36 ፐርሰንቱ ሚድያዎች እና ጋዜጠኞች በአንፃራዊነት የሀሰተኛ መረጃዎችን በብዛት ሲያሰራጩ ማየታቸውን ጠቁመው ነበር።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::