ኢትዮጵያ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች?

ኢትዮጵያ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች?

መጋቢት 14፣ 2016

በጋና አክራ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው እና ዛሬ በሚጠናቀቀው 13ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋን በሚገልጽ መልኩ መረጃዎች በስፋት ሲጋሩ ተመልክተናል።

ነገር ግን ኢትዮጵያ 18 ሜዳሊያ በማግኘት 2ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው የውድድሩን የአትሌቲክስ ዘርፍ ብቻ ሲሆን አትሌቲክስ ሩጫ፣ ዝላይ እና ውርወራን የሚያካትት የስፖርት ዘርፍ ነው።

በሌላ በኩል መላ አፍሪካ ጨዋታዎች አትሌቲክስን ጨምሮ በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮች የሚካሄዱበት ሲሆን ከነዚህ መካከልም ባዲመንተን፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቦክስ፣ ቼዝ፣ ዋና፣ ቴኒስ፣ ነጻ ትግል እና ብስክሌት ውድድር ይገኙበታል።

በዚሁ መሰረት የአፍሪካ ጨዋታዎችን የሜዳልያ ሰንጠረዥ ግብጽ 187 ሜዳልያዎችን በማግኘት ስትመራ ናይጄሪያ በ121 ሜዳልያ ትከተላለች።

ኢትዮጵያ ደግሞ በአትሌቲክስ 18፣ በቦክስ 3 እና በብስክሌት ውድድር ባገኘችው አንድ ሜዳልያ በድምሩ በ22 ሜዳልያዎች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የዚህን ዝርዝር መረጃም ከውድድሩ ድረ-ገጽ መመልከት ይቻላል፡ https://results.accra2023ag.com/wrs/eng/zz/engzz_general-medal-count.htm

ስለዚህ ኢትዮጵያ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::