ከአውድ ውጭ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምስሎች ለተዛባ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ እንጠንቀቅ!

ታህሳስ 03፣ 2016 ዓ.ም

ብዙዎቻችን በማህበራዊ ሚዲያ ከምናጋራቸው የጽሁፍ መረጃዎች ጋር ምስሎች ን እናያይዛለን። ይህንን የምናደርገውም ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት፣ የምናጋራውን መረጃ ታማኝነት ለመጨመር ወይም ትኩረት ለመሳብ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው አሰራር በመደበኛው የጋዜጠኝነት ሙያም የተለመደ አሰራር መሆኑን ይታወቃል።

በጽሁፍ ከምናስተላልፋቸው መረጃው ጋር የምናያይዛቸው ምስሎች ተገቢውን መልዕክት ሊያስተላልፉ የሚችሉት አውዳቸውን የጠበቁ ከሆኑ ብቻ ነው። ነገር ግን ምስሎች ከአውድ ውጭ ከቀረቡ ማለትም የቆዩ ወይም ከሌላ ቦታ የተወሰዱ ከሆኑ ግን መረጃ የማዛባት እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል።

ይህ ማለት በጽሁፍ የቀረበው መረጃ ትክክለኛ ሆኖ ነገር ግን ከአውድ ውጭ በተወሰደ ምስል ከታጀበ በእውነታው ላይ ግነት በመጨመር ወይም የተሳሳተ እይታ በመፍጠር የመረጃ መዛባት ይፈጥራል። በአንጻሩ በጽሁፍ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ ሆኖ በተጨማሪ ከአውድ ውጭ በተወሰደ ምስል ከታጀበ ብዥታንና ማደናገርን በመፍጠር በሀሠተኛ መረጃ የመጋለጥን እድል ይጨምራል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምስሎች በማሳመን ረገድ ያላቸው ኃይል ከፍተኛ መሆኑ ነው። በግንዛዜ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የሳይኮሎጅ (Cognitive Psychology)  ጥናቶች እነደሚጠቁሙት ሰዎች በምስል  ታጅበው የሚቀርቡ መረጃዎችን የማመን ዝንባሌያቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በምስል  ታጅበው የሚቀርቡ መረጃዎች ከፍተኛ ትኩረት የመሳብ ኃይል ያላቸው ሲሆን መልሰው የመጋራት እድላቸው ከፍ ያለ ነው። አዶቤ በፌስቡክ በሚጋሩ መረጃዎች ዙሪያ ያደረገው አንድ ጥናት በምስል  ታጅቦ የሚጋራ ጽሁፍ፤ ካለፎቶ ከሚጋራ ጽሁፍ አንጻር በሶስት እጥፍ ግብረመልስ የማግኘት እድል አሳይቷል።

ለምሳሌ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ቢሸፍቱ አቅራቢያ ‘የኤርፖርት ሲቲ’ እንደሚገነባ መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ በርከት ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች የኤርፖርት ሲቲውን ያሳያሉ ያሏቸውን ምስሎች ሲያጋሩ ተመልክተን ነበር። ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ፍተሻ የተጋሩት ምስሎች ከአውድ ውጭ የተወሰዱ መሆናቸውን በማረጋገጥ ዘገባ ሰርቶም ነበር። እንዲህ ያሉት ከአውድ ውጭ በተወሰዱ ምስሎች የሚታጀቡ መረጃዎች ሀሠተኛ እይታን በመፍጠር የመረጃ መዛባትን የሚፈጥሩ ናቸው። በተመሳሳይ ከርሃብ፣ ሞት፣ ግጭት እና መፈናቀል ጋር በተያያዘ ከሚጋሩ መረጃዎች ጋርም ከአውድ ውጭ የሚወሰዱ ፎቶዎች አብረው እንደሚያያዙ ባለፉት አመታት የታዘብነው ነው።

ስለሆነም በማህበራዊ ሚዲያ የምናያቸውን መረጃዎች ከማመናችን በፊት ተያይዘው የቀረቡ ምስሎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ይኖርብናል። ምስሎች ከአውድ ውጭ የቀረቡ ናቸው የሚል ጥርጣሬ ካደረብን በምልሰት ምስል መፈለጊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም እናረጋግጥ። የመተግበሪያዎን አጠቃቀም ለመረዳት ኢትዮጵያ ቼክ ያሰናዳቸውን ቪዲዮዎች የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች በመከተል ይመልከቱ:

የጉግል መተግበሪያን በመጠቀም ምስሎችን በምልሰት መመርመር እንዴት ይቻላል?:

የቲንአይ መተግበሪያን በመጠቀም ምስሎችን መመርመር እንዴት ይቻላል?:

የ Yandex መተግበሪያን በመጠቀም ምስሎችን በምልሰት መመርመር እንዴት ይቻላል?:

ከአውድ ውጭ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምስሎች ለተዛባ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ እንጠንቀቅ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::