አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተናገሩት ተብሎ የተጋራው መረጃ የቆየና ከአውድ ውጭ የቀረበ ነው

ታህሳስ 21፣ 2016 ዓ.ም

ከ64,100 በላይ ተከታዮች ያሉትና “ኢትዮጵያዊ’’ የሚል ስያሜ ያለው የቲክቶክ አካውንት  ‘’ታዋቂው የንግድ ሰው ኤርሚያስ አመልጋ የአብይ አህመድ መጨረሻ ሳይታወቅ ምንም አይነት ቢዝነስ መጀመር አያስፈልግም ብሏል’’ የሚል መረጃ ማጋራቱን ተመልክተናል። ከመረጃው ጋርም አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ሲናገሩ የሚደመጥበት አጭር ቪዲዮ ተያይዟል።

አቶ ኤርሚያስ በንግግራቸው ‘’በአሁኑ ወቅት ጸጥ ብሎ፣ አንገትን ደፋ አድርጎ ነገሮች ወዴት እንደሚሄዱ ማየት ነው እንጅ አዲስ ስራ ጀምሩ ብየ በአሁኑ ጊዜ ለመምከር ይከብደኛል። May be ወቅቱ ከፈጠራቸው ሁናቴዎች ጋር ተያይዞ የሚመጡ ዕድሎች ካሉ እነሱን ማየት ይቻላል፤ እነሱም ቢሆኑ ጊዜዊ እንጅ ዘላቂ አይመስሉኝም…” ሲሉ ይደመጣሉ።

ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ማጣራት ከላይ የተጠቀሰው ቪዲዮ የቆየና የአቶ ኤርሚያስ ንግ ግርም ከአውድ ውጭ የቀረበ መሆኑን አረጋግጧል። አቶ ኤርሚያ በቪዲዮው ላይ የሚደመጠውን መልዕክት ያስተላለፉት የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በተከታታይ በዩቱብ በለቀቋቸው ትምህርታዊ ቪዲዮዎች ነበር። ‘’ቢዝነስ ጀምሩ ብየ አልመክርም’’ ያሉትም የወረርሽኙን ወቅት ግንዛዜ ውስጥ በማስገባት ነበር።

በወቅቱ ተከታታይ ቪዲዮዎቹን የጫነው የዩቱብ ቻናል  አገልግሎቱን ያቆመ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሰው መልዕክት የሚታይበትን ቪዲዮ ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል መግኘት ይቻላል: https://www.youtube.com/watch?v=VvjRKnsySCE

የኹነቶችን ጊዜ ሳይጠቅሱ እንዲሁም ከአውድ ውጭ የሚጋሩ መረጃዎች ለሀሠተኛና ለተዛቡ መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ  ጥንቃቄ እናድርግ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::