በአዲሱ ዓመት በማህበራዊ ሚዲያ የሚታዩ የአሉታዊ ይዘቶችን ስርጭት እና ጉዳት ለመቀነስ የበኩላችንን አስተዋጾ እናድርግ!

twitter verification

ጳጉሜ 06፣ 2015 ዓ.ም

እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ ዛሬ በሚጠናቀቀው 2015 ዓ.ም ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የጥላቻ መልዕክቶች፣ የሴራ ትንተናዎች፣ የማጭበርበር ድርጊቶች እና ሌሎች አሉታዊ ይዘቶች በማህበራዊ ሚዲያ በርከት ብለው የታዩበት ነበር። ይህም መሬት ላይ ወርዶ ቀላል በማይባል ደረጃ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የፖለቲካ ምስቅልቅሎችን እንዳባባሰ ይገመታል።

ኢትዮጵያ ቼክም እነዚህን ቀውስ ፈጣሪና አባባሽ አሉታዊ ይዘቶችን ለመከላከልና ተደራሽነታቸውን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን የሰራበት ዓመት ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን አጣርተናል፣ ከአውድ ውጭ የቀረቡ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን ፈትሸናል፣ ተመሳስለው የተከፈቱ ሀሠተኛ አካውንቶችን አጋልጠናል።

እንዲሁም የዜጎችን የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ያሳድጋሉ ብለን ያሰብናቸውን ማብራሪያዎች እና መልዕክቶች በጽሁፍ፣ በምስልና በቪዲዮ በማስደገፍ ያደረስንበት ዓመት ነበር። በተመሳሳይ የጋዜጠኞችን መረጃ የማጣራት ክህሎት ለማጎልበት የሚረዱ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ስልጠናዎችን ሰጥተናል። ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሀሠተኛ መረጃ እና ከጥላቻ መልዕክቶች አንጻር የነቁና የበቁ እንዲሆኑ የሚያስችል የሙከራ መርሐ ግብር የጀመርንበት ዓመት ነበር።

ተለዋዋጭ የሆነውን የአሉታዊ ይዘቶችን ባህሪ ለመረዳትና እንዲሁም ሌሎች እንዲረዱ ለማድረግ ብዙ ተጉዘናል። ለዚህም የሚረዱ አዳዲስ ዘዴዎችንና የቴክኖሎጅ ውጤቶች ለማስተዋወቅም ሞክረናል። ተደራሽነታችንን ለማስፋትም ከፌስቡክ፣ ከኤክስ የቀድሞው ትዊተር፣ ከቴሌግራም፣ ከዩቱብ በተጨማሪ የቲክቶች ቻናል ከፍተናል። የሚዲያ ክትትል ና ቅኝት ስራችንንም በተመሳሳይ አስፍተናል።

በሶስት ቋንቋዎች (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና ትግርኛ) የሰራናቸውን ከላይ የተገለጹ ተግባራት የከወነው በጣት በሚቆጠሩ ባለሙያዎች እና ባነስ በጀት በጀት ነበር። መረጃ የማግኘት እክሎችና የቴሌኮም አገልግሎት መስተጓጎልም የበለጠ እንዳንሰራ ከፈተኑን ነገሮች ይጠቀሳሉ።

ይሁንና በርከት ያሉ ችግሮችና ተግዳሮቶች ቢኖሩም በአዲሱ ዓመት ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የጥላቻ መልዕክቶች፣ የሴራ ትንተናዎች፣ የማጭበርበር ድርጊቶች እና ሌሎች አሉታዊ ይዘቶችን የመከታተልና የማጋለጥ ስራችንን አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል። የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት ላይ የሚያተኩሩ ማብራሪያዎችንና መልዕክቶችንም በተሻለ ሁኔታ ማጋራታችን ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮችም በአዲሱ ዓመት በማህበራዊ ሚዲያ የሚታዩ የአሉታዊ ይዘቶችን ስርጭት እና ጉዳት ለመቀነስ የበኩላችሁን አስተዋጾ በተሻለ ሁኔታ የምታበረክቱበት እንደሚሁን ተስፋችን ነው።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::