የኤችአይቪ ‘መድኃኒት ተገኝቷል’ በሚል እየተሰራጨ ከሚገኝ አሳሳች መረጃ እንጠንቀቅ!

misleading information that is being spread about the HIV 'cure

ህዳር 23፣ 2016 ዓ.ም

ከሰሞኑ የኤችአይቪ /HIV/ ‘መድኃኒት ተገኝቷል’ የሚል መረጃ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተሰራጨ ይገኛል።

በተለይ ጥቂት የማይባሉ የፌስቡክ ገጾችና የዩትዩብ ቻነሎች የአንባቢዎችን እንዲሁም ተመልካቾችን ትኩረት የሚስቡ ርዕሶችን በመጠቀም ጉዳዩን ሲዘግቡ ተመልክተናል።

ይሁን እንጂ ይህ መነጋገሪያ የሆነው መድኃኒት ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችን ከቫይረሱ ነጻ እንደሚያደርግ ተደርጎ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጋራ መረጃ የተሳሳተ ነው።

ፕሪ ኤክስፖዠር ፕሮፍላክሲስ (Pre-exposure prophylaxis) ወይም በምህጻረ ቃል ፒአርኢፒ (PrEP) የሚል መጠሪያ ያለው መድኃኒት ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ሰዎች በቫይረሱ እንዳይጠቁ የሚከላከል ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መድኃኒቱ ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ሰዎችን በቫይረሱ የመጠቃት እድል የሚቀንስ መሆኑን በድረ-ገጹ አስተምጧል፡ https://www.who.int/teams/global-hiv-hepatitis-and-stis-programmes/hiv/prevention/pre-exposure-prophylaxis

ይህ ፒአርኢፒ በመባል የሚታወቀው መድኃኒት አዲስ ከሰሞኑ የተገኘ ሳይሆን ባለፉት አመታት ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ እንደሆነም ይህ የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።

የሰሞኑ የጥናት ውጤት ምንድነው?

ሰሞነኛው ለኤችአይቪ ‘መድኃኒት ተገኘቷል’ የሚል መረጃ መነሻ በዩናይትድ ኪንግደም (UK) ውስጥ የተደረገና ሰሞኑን ይፋ የተደረገ የጥናት ውጤት ነው።

ጥናቱን በዋናነት የመራው የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የጤና ደኅንነት ኤጀንሲ ሲሆን ጥናቱም የፒአርኢፒ መድኃኒትን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የተደረገ ነበር።

ጥናቱ አኤአ ከጥቅምት 2017 እስከ ሐምሌ 2020 የተደረገ ሲሆን 24 ሺህ ሰዎች መድኃኒቱን በመውሰድ በጥናቱ ተሳትፈዋል።

በጥናቱ ውጤት መሰረትም ፕሪ ኤክስፖዠር ፕሮፊላክሲስ (PrEP) በኤችአይቪ የመያዝ እድልን በ86% የሚቀንስ ሲሆን በክሊኒካል ሙከራ ደግሞ 99% ውጤታማ መሆኑ ተነግሯል።

በዩኬ የጤና ደኅንነት ኤጀንሲ መሪነት ተደርጎ ሰሞኑን ይፋ የሆነው ጥናት በላንሴት መጽሔት ድረ-ገጽ የታተመ ሲሆን በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል፡ https://www.thelancet.com/journals/lanhiv/article/PIIS2352-3018(23)00256-4/fulltext

በተሳሳተ መልኩ የሚቀርቡ ጤና ነክ መረጃዎች ለተሳሳቱ ዉሳኔዎች እና የጤና ችግሮች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ አምነን ከመቀበላችን በፊት ትክክለኛነታቸውን እናረጋግጥ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::