እስራኤል ኤምባሲ ለመግባት ተጨማሪ ቀጠሮ ያዙ ተባልን ያሉ ሰዎች ጉዳይ

ሰኔ 14፣ 2015 ዓ.ም

  • “እስራኤል ኤምባሲ ለቪዛ ጉዳዮች ለመግባት ስንፈልግ ጥበቃዎች በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ ኢንተርኔት ካፌ ሄዳችሁ ሌላ ፎርም ሙሉ እያሉን ነው”— ቅሬታ አቅራቢዎች
  • “ቀጠሮ ለማስያዝ ገንዘብ የሚቀበል ማንኛውም አካል የኤምባሲው አይደለም፣ ወይም የኤምባሲው ፈቃድ የለውም”— የእስራኤል ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ቼክ

በቅርብ ቀናት በርካታ ግለሰቦች በኦንላይን ቀጠሮ ይዘው ወደ እስራኤል ኤምባሲ ለቪዛ ጉዳይ ቢያመሩም በስፍራው የሚገኙ የጥበቃ ሰራተኞች አንድ በአካባቢው ወደሚገኝ እና “ካሱ ኢንተርኔት” ወደሚባል የኢንተርኔት ካፌ እንዲሄዱ እና ሌላ ቀጠሮ እንዲይዙ እየተነገራቸው እንደሆነ ለኢትዮጵያ ቼክ አሳውቀዋል።

እነዚህ ጠቋሚዎች እንደሚሉት ራሳቸው ቀጠሮ የያዙበትን ወረቀት ለጥበቃዎቹ ቢያሳዩም “ትክክለኛ ዌብሳይት ላይ ቀጠሮ አልያዛችሁም” የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው እንዲመለሱ እየተደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፣ በተደጋጋሚም ወደዚህ ኢንተርኔት ካፌ ሄደን እና 150 ብር ከፍለን ሌላ ቀጠሮ እንድንይዝ ተጠይቀናል ብለዋል።

በዚህ ምክንያት ሰዎች ከትምህርት፣ ህክምና እና የሀይማኖት ጉዞዎች እየተስተጓጎሉ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የኤምባሲው ምላሽ

ኤምባሲው በዚህ ዙርያ ለኢትዮጵያ ቼክ ባደረሰው የኢሜይል መልዕክት ቀጠሮ ለማስያዝም ሆነ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመግባት ክፍያ አይጠየቅም ብሏል።

ኤምባሲው አክሎም “ግቢ ውስጥ ለመግባት የሚቻለው በኦንላይን ወይም በስልክ ቀጠሮ ሲያዝ ብቻ ነው። ቀጠሮ ለማስያዝ ግን ገንዘብ የሚቀበል ማንኛውም አካል የኤምባሲው አይደለም፣ ወይም የኤምባሲው ፈቃድ የለውም” ብሏል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::