በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚፈበረኩ እውነት መሳይ ምስሎች ለሀሠተኛ መረጃ እንዳያጋልጡን እንጠንቀቅ!

Images developed by AI

ህዳር 13፣ 2016 ዓ.ም

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅዎች የሚፈበረኩ ምስሎች በኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ከባቢ በስፋት ሲዘዋወሩ መመልከት የተለመደ ሆኗል።

ምስሎቹ እንደ ዳል ኢ (DALL-E)  ባሉ ለአውድ እና ለእውነታ የተጠጉ ምስሎችን በሚፈበርኩ የሰውሰራሽ አስተውሎት መገልገያዎች የተሰሩ ሲሆን የብዙ ሰዎችን ቀልብ መሳባቸውን ለማወቅ የመጋራት ምጣኔያቸው እና ተደራሽነታቸውን መመልከት በቂ ነው።

በስፋት ከተዘዋወሩት ምስሎች መካከልም በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እንቅስቃሴን፣ የኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) የታንዛኒያ ቆይታን፣ የገርአልታ ታሪካዊና መልከዓምድራዊ ገጽታን፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ብሶቶችን ብልጽግናን ግብ ያደረጉ የልማት ዘመቻዎችን እንዲሁም ወደብና የባህር ኃይል መርከቦችን ለማሳየት የሞከሩትን መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ ምስሎች የብዙዎችን ቀልብ ይሳቡ እንጅ አብዛኞቹ በሰውሰራሽ አስተውሎት መገልገያዎች የተሰሩ መሆናቸውን በቀላሉ መለየት ይቻላል። ለዚህም በምስሎቹ ላይ የሚታዩ በርካታ ዝንፈቶችንና መደበላለቆች ማስተዋል በቂ ነው። በአንጻሩ ጥቂቶቹ ለእውነታውና ለአውዱ በእጅጉ ከመቅረባቸው የተነሳ መደናገር መፍጠር ችለዋል።

ሆኖም ይህ የቴክኖሎጅው የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ምስል ፈብራኪ መገልገያዎች በየዕለቱ ከባቢያዊ አውዱን ይበልጥ እየተማሩ እንዲሁም የማሰላሰል አቅማቸውን የሚያጎለብት ዳታ ክምችት ከፍ እያለ ሲሄድ በእውነት እና በሀሰት መካከል ግርዶሽ መፍጠራቸው የማይቀር መሆኑ እሙን ነው። ለዚህ ደግሞ የተሻለ የዳታ ክምችት በሚገኝባቸው ጉዳዮች አኳያ ለእውነት እጅግ የቀረቡ ምስሎችን መፈብረክ መቻላቸውን መጥቀስ ይቻላል።

ይህም በመላው ዓለም ስጋት የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል። መገልገያዎቹ  እየጎለበቱ በሄዱ ቁጥር የሚፈበርኳቸው ምስሎች በእውነትና በሀሠት መካከል ያለውን መስመር በመጋረድ ለሰላም መደፍረስና ለስርዐት መናጋት ይውላሉ ብለው የሰጉ አካላትም መፍትሄ ለማበጀት ላይ ታች ማለት ከጀመሩም ቆይተዋል።

ከዚህ አንጻር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ጉዳዩን በተመለከተ የሚያማክራቸው አለም አቀፍ የባለሙያዎች ስብስብ ማዋቀራቸው ይታወቃል። ድርጅታቸውም የሰውሰራሽ አስተውሎ ቴክኖሎጅን የሚቆጣጠር ገለልተኛ ኤጀንሲ ለማቋቋም መወጠኑን ከወራት በፊት ማስወቁ ይታወቃል።

ቴክኖሎጅውን የሚበለጽጉ ኩባንያዎችም ስጋቶችን ተረድተው የመፍትሄ እርምጃዎችን እንዲዎስዱ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸው ሲሆን ኦፕንኤአይ፣ አማዞን፣ ጎግል፣ ሜታ እና ማይክሮሶፍት በሀምሌ ወር ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር ባደረጉት ምክክር ስጋቶችን የሚቀርፉ አሰራሮችን ለመተግበር ፍቃዳቸው ገልጸው ነበር። በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚፈበረኩ ምስሎችን ለመለየት የሚረዱ የጽሁፍ ምልክቶችን ማስቀመጥ በመፍትሄነት ቃል ከተገቡት መካከል ይገኝበታል።

ይህን ተከትሎም ጎግል በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ የተፈበረኩ ምስሎችን ለመለየት የሚያስችል መገልገያን ወደስራ ለማስገባት ሙከራ መጀመሩን አስታውቋል። ይህ ሲንትአይዲ (SynthID) የሚል መጠሪያ የተሰጠው መገልገያ በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅ የተፈበረኩ ምስሎችን በቀልሉ መለየት እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል። መገልገያው ኢሜጅን (Imagen) በተሰኘው የጎግል የሰውሰራሽ አስተውሎት መገልገያን የተመረቱ ምስሎችን በመለየት ስራ እንደሚጀምርም ተነግሯል።

በተመሳሳይ ቲክቶክ እንዲህ ያሉ ምስሎችን ለመለየት የሚያስችል ቴክኖሎጅን ወደስራ እንደሚያስገባ የገለጸ ሲሆን ጉዳዩን በተመለከተም ከወራቶች በፊት ጠበቅ ያለ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል።

ስጋቶቹን የሚቀርፉ መፍትሄዎች በአግባቡ ወደስራ እስከሚገቡ ግን ያለው አማራጭ የቴክኖሎጅውን የዕለት ከዕለት እድገት በመገንዘብ ለአሉታዊ ይዘቶች ላለመጋለጥ ንቁ ሆኖ መጠበቅ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::