በኢትዮ 360 ሚዲያ የተሰራጨ አሳሳች ምስል

image shared out of context by Ethio 360 media

ሚያዝያ 04፣ 2015

ይዘቶቹን በዩትዩብ የሚያሰራጨው ኢትዮ 360 ሚዲያ “በአማራ፣ በአፋር፣ በሱማሌ እና በጋምቤላ እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት” በሚል ርዕስ በትናንትናው ዕለት ባቀረበው የቀጥታ ስርጭት በበርካታ ቶዮታ-ቴክኒካል ተሽከርካሪዎች የተጫኑ የፌዴራል ፖሊሶች የሚታዩበትን ፎቶ ማጋራቱን ተመልክተናል።

ይህ ፎቶ በዚህ ፕሮግራም ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ከፕሮግራሙ አቅራቢዎች አንዱ በተሽከርካሪዎች ላይ ተጭነው የሚታዩት ወታደሮች ባለፉት ቀናት በአማራ ክልል ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በክልሉ የተሰማሩ ባለቀይ ቦኔት ወታደሮች መሆናቸው ሲገልጽ ይደመጣል፣ የወታደሮቹ ማንነትም ተጠቅሷል።

ምንም እንኳን ባለፉት ቀናት የፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች በአማራ ክልል መሰማራታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ሚዲያዎች መዘገባቸው የሚታወቅ ቢሆንም ኢትዮ 360 ያጋራው ምስል የቆየና ከአውድ ውጭ የቀረበ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

ትክክለኛው ፎቶ እ.አ.አ ጥር 18 ቀን 2023 ዓ.ም በፌዴራል ፖሊስ ኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጽ የተጋራ ነው። ከፎቶው ጋርም የፌዴራል ፖሊስ የአዳዲስ ትጥቆች ባለቤት መሆኑን የሚገልጽ ዜና ተያይዞ ይነበባል።

ትክክለኛውን ፎቶ ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ማግኘት ይቻላል: https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid02H3iDr8N9gPYcoSDGXL19vroxP3PSAcDLhKepc2hjFUKtLBRPnYtEWDMUrpiTcPicl&id=100064451782216&sfnsn=mo&mibextid=DcJ9fc

ከአማራ ክልል ልዩ ሃይል የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጋር በተያያዘ ከባለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ መሆኑና የፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች መሰማራታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች በተለያዩ ሚዲያዎች በመጋራት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::