አማተር የመረጃ አጣሪ በመሆን እንዴት በጎ አስተዋጾ ማበርከት እንችላለን?

አማተር የመረጃ አጣሪ

ሰኔ 22፣ 2015 ዓ.ም

በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎች፣ የማጭበርበር ድርጊቶች፣ የሴራ ትንተናዎች እና የጥላቻ መልዕክቶች በሀገር እና በዜጎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግር በየዕለቱ የምንታዘበው ሃቅ ነው። ይህን አያሌ አሉታዊ ውጤቶችን በማስከተል ላይ የሚገኝን ችግር ለመዋጋት ኢትዮጵያ ቼክ እና ሌሎች ጥቂት የመረጃ አጣሪ ተቋማት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ይሁንና ከችግሩ ስፋትና ከመረጃ አጣሪ ተቋማት የአቅም ውስንነት አኳያ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሁሉም ዜጋ አስተዋጾ ወሳኝ መሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ነው። እርስዎም እንደ አንድ ሀላፊነት የሚሰማው ዜጋ አማተር የመረጃ አጣሪ በመሆኑ በጎ አስተዋጾ ማበርከት ይችላሉ። በተለይም ለእርስዎ በቦታ፣ በጊዜና በስነልቦና ቅርብ በሆኑ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ! ይህንንም በቀላል ወጭ እና የግልዎን የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶች፣ ገጾችና ቻናሎች በመጠቀም መከወን ይችላሉ።

አማተር የመረጃ አጣሪ ለመሆን በመጀመሪያ መሰረታዊ የሆኑ የመረጃ ማጣራት ክህሎቶችን እና የስነምግባር መርሆችን መማር ይጠበቅበዎታል።

የመረጃ ማጣራት በመሠረታዊነት ሶስት ሂደቶችን ይከተላል። እነርሱም ሊጣራ የሚችለውን መረጃ መለየት፣ መረጃውን ማጣራትና ብያኔ መስጠት ናቸው።

ሊጣራ የሚችለውን መረጃ መለየት የሚዲያ ክትትልና ቅኝት (media monitoring) ከማድረግ እና ከመጠርጠር ይጀመራል። እንደ አማተር የመረጃ አጣሪ ሊጣራ የሚችል መረጃን በቀላሉ ከምንከታተላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶች፣ ገጾችና ቻናሎች ማግኘት እንችላለ። በዚህም ሀሠተኛ ወይም የተዛባ መረጃ ወይም የማጭበርበር ድርጊት ሊሆን ይችላል በሚል የጠረጠርነውን ይዘት ቆም ብለን መመርመር ይጠበቅብናል። በተለይም ጉዳዩ በቦታ፣ በጊዜና በስነልቦና እርስዎ ከሚኖሩበት አካባቢ ቅርበት ካለው ለማጣራት ይወስኑ።

በመቀጠልም መረጃውን ወደማጣራት ይግቡ። መረጃውን ለማጣራት በቅድሚያ የመጀመሪያ ደረጃ የመረጃ ምንጮችን ይጠቀሙ። ለዚህም ሊጣራ በሚችለው መረጃ የተጠቀሱ አካላት ካሉ እነርሱን ያናግሩ። በተጨማሪም ሊጣራ የሚችለውን መረጃ ለማመሳከር ጠቃሚ ይሆናሉ ብለው ያሰቧቸውን ሰዎች፣ ተቋማት ወዘት ያነጋግሩ፤ ሰነዶችን ይፈትሹ።

ሊጣራ የሚችለው መረጃ በፎቶና በቪዲዮ መልቅ የቀረበ ሆኖ፣ ከአውድ ውጭ ጥቅም ላይ የዋለ፣ የተነካካ ወይም ፎቶሾፕ የተደረገ ነው ብለው ካመኑ የመረጃ ማጣሪያ መተግበሪያዎችን ይጠቀሙ። ለዚህም እንደ ጎግል ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች፣ ትይኒኣአይ፣ ያንዴክ፣ ፎቶ ፎረንሲክ ያሉ መገልገያዎች ይረዳዎታል። ስለመገልገያዎች ኣአጠቃቅመም የበለጠ ለማወቅ በኢትዮጵያ ቼክ የዩቱብ ቻና የቀረቡ የመማሪያ ቪዲዮዎችን ይመልከቱ።

መረጃውን ካጣሩ በኃላ ስለትክክለኛነታቸው ብይን ይስጡ። ከዚያም ቀለል ባለ ቋንቋ በመጠቀም በፌስቡክ ገጽዎ ወይም በትዊተር አካውንትዎ ወይም በቲክቶክ ቻናልዎ ወይም በዩቱብ ቻናልው አልያም በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶችው ያጋሩ። ይህንን ሲያደርጉ መረጃውን ለማጣራት የተጠቀሙበትን ሂደትና የመረጃ ምንጮችዎን በግልጽ ይናገሩ።

በአማተር የመረጃ አጣሪነትዎ የበለጠ ታማኝነትና ተቀባይነት ለማግኘ የሙያውን የስነምግባር መርሆች ሁሌም መከተልዎን መዘንጋት አይገባም። የመረጃ ማጣራት መሰረታዊ የስነምግባር መርሆዎች የሚባሉትም እውነተኝነት፣ ተጠያቂነት፣ ነጻነት፣ ፍትሃዊነት እና ግልጽነት ናቸው።

አማተር የመረጃ አጣሪ በመሆንበግል የማህበራዊ ሚዲያ አካውንትዎ የመረጃ ማጣራት ስራ በመከውን በጎ አስተዋጽዎ ያድርጉ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::