ከአውድ ውጭ የተወሰዱ ፎቶዎችን ለመልየት የሚረዱ ፍንጭ ሰጭ መረጃዎች

ከአውድ ውጭ የተወሰዱ ፎቶዎችን ለመልየት የሚረዱ ፍንጭ ሰጭ መረጃዎች

ሐምሌ 13፣ 2015

ሀሠተኛና የተዛቡ መርጃዎች ከሚሰራጩባቸው መንገዶች መካከል ከአውድ ውጭ የሚቀርቡ ፎቶዎች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። ከአውድ ውጭ የሚቀርቡ ፎቶዎች ድርጊቱ ከተፈጸመበት ቦታ ውጭ የተወሰዱ ወይም የቆዩ ሲሆኑ እነሱንም ለመለየት የተለያዩ መገልገያዎችን (tools) እንጠቀማለን።

ከምንጠቀምባቸው መገልገያዎች መካከል በምልሰት ፎቶዎችን ለመለየት የሚረዱን እንደ ጎግል ኢሜጅ፣ታይኒአይ እና ያንዴክስ የመሳሰሉ የሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች ያሉ መገልገያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ፎቶዎች የተነሱበት ቦታ በትክክል ለማወቅ የጅኦሎኬሽን አገልግሎት የሚሰጡ መገልገያዎችን ጥቅም ላይ እናውላለን። ለዚህም የጎግል ካርታን እና የጎግል ኸርዝ መገልገያዎችን በምሳሌነት ማንሳት እንችላለን። እንደሰንካልክ (SunCalc) ያሉ ወቅት ጠቋሚ መገልገያዎችም ከአውድ ውጭ የተወሰዱ ፎቶዎችን ለመለየት አገልግሎት ላይ ይውላሉ።

መገልገያዎቹ ተፈላጊውን ምላሽ ሳይሰጡን ሲቀሩ በፎቶዎች ላይ የሚታዩ መረጃ ሰጭ ፍንጮችን በማስተዋልና በመመርመር ፎቶዎች የተወሰዱበትን አውድ ለመገመት ጥረት ማድረግ ከሀሠተኛና ከተዛባ መረጃ ሊታደገን ይችላል። ፍንጭ ከሚሰጡ መረጃዎች መካከል ወቅቶችና መልክዐ ምድሮች በዋነኝነት መጥቀስ ይቻላል።

በፎቶዎቹ ላይ የሚታዩ ወቅት ጠቋሚ ማለትም የሰብልና የእጽዋት እንዲሁም የሰማይና የአፈር ቀለማት፣የአካባቢው እርጥበት፣ የሰዎች አለባበስ ወዘተ ምስሉ ስለተወሰደበት ጊዜ ፍንጭ ይሰጡናል። ይህም በነሀሴ ወርየተነሳን ፎቶ በጥር ወር ከተነሳ ፎቶ በቀላሉ ለመለየት ያስችለናል። ለምሳሌ በያዝነው የሀምሌ ወር በሰሜን ሸዋዞን የፈጸመን ድርጊት ያሳያል ተብሎ የተጋራን ፎቶ በፎቶው ላይ የሚታዩ ወቅት ጠቋሚ ፍንጮን በመመርመር ስለ ትክ ክለኛነቱ መገመት እንችላለን።

በተመሳሳይ በፎቶዎች ላይ የሚታዩ መልክዐ ምድር ጠቋሚ ፍንጮች ምስሉ የተወሰደበትን ቦታ ለመገመት ጠቃሚ መረጃ ይሰጡናል። በፎቶዎች ላይ የሚታየው መልክዐ ምድር ተራራማነት ወይም ሜዳማነት፤ ልምላሜ ወይም ደረቃማነት መረጃ ከሚሰጡ ፍንጮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በፎቶው ላይ የሚታዩ የእጽዋትና የሰብል አይነቶችም መረጃ ፍንጭ ሊሰጡ ይችላሉ። ለምሳሌ በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመን ድርጊት በአፋር ክልል እንደተደረገ በማስመሰል የቀረበን ፎቶ በፎቶው ላይ የሚታዩ የእጽዋት አይነቶችን በደንብ በማስተዋል ሀሠተኛ መሆኑን ለመገመት እንችላለን። በተመሳሳይ በትግራይ ክልል የተወሰደን ፎቶ በምስራቅ ጎጃም ከተወሰደ ፎቶ መለየት ያስችለናል።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚጋሩ ፎቶዎች ላይ የሚታዩ ፍንጭ ሰጭ መረጃዎችን በደንብ በማስተዋልና በመመርመር እራሳችንን ከሀሠተኛና ከተዛቡ መረጃዎች እንጠብቅ!

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::