በማህበራዊ ሚዲያ ከሚጋሩ አሳሳች እና ሳይንሳዊ መሰረት ከሌላቸው የጤና መረጃዎች እራሳችንን እንጠብቅ!

የጤና መረጃዎች

መስከረም 06፣ 2015 ዓ.ም

አሁን አሁን እራሳችንንም ሆነ የቅርብ ሰዎቻችን የህመም ስሜት ሲሰማቸው ፈውስ ለማግኘት ወደህክማና ተቋማት ከመሄድ ይልቅ ወደተንቀሳቃሽ ስልካችን ወይም ላፕቶፓችን ማማተር የተለመደ ድርጊት ሁኗል። ምናልባት ይህን ምናደርገው ከጊዜና ከገንዘብ አኳያ ቀላልና ርካሽ አማራጭ ስለሆን ይሆናል። ሆኖም ይህ ልምዳችን እስከሞትና ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስ ለሚችል ጉዳት ሊያጋልጠን ይችላል።

የአለም ጤና ድርጅት በተደጋግሚ እንደገለጸውና በርከት ያሉ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢንተርኔት ከሚጋሩ ጤና ነክ መረጃዎች መካከል ቀላል የማይባሉት አሳሳችና ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው የመሆን እድላቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ባሉት አሳሳችና ሳይንሳዊ መሰረት በሌላቸው የጤና መረጃዎች ሳቢያም ቀላል የማይባሉ ሰዎች ዘላቂ ጉዳት ደርሶባቸው ምስክርነታቸው ሲሰጡ መመልከትም የተለመደ ሆኗል።

አሳሳችና ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸውን ጤና ነክ መረጃዎች በስፋት ከሚሰራጩባቸው የማህበራዊ ሚዲያዎች መካከል ዩቱብ፣ ቲክቶክና ቴሌግራምን በቀዳሚነት ስማቸው የሚጠቀስ ሲሆን ችግሩ ባሳሰባቸው ግለሰቦችና ተቋማት ግፊትና ውትወታ አንዳንዶቹ የእርምት እርምጃ መውሰድ ጀመረዋል። ለምሳሌም ዩቱብ ከጤና አኳያ የሚጋሩ መረጃዎችን አሳሳችነትና አደገኛነት ለመቀነስ ጠበቅ ያለ የፖሊሲና የመርህ ማሻሻያ ማድረጉን ከሳምንታት በፊት አስታውቋል። እንዲሁም በአንዳንድ ሀገሮች የጤና ይዘት ለሚያቀርቡ የህክምና ባለሙያዎች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ባጅ መስጠት መጀመሩ በስፋት ተዘግቧል።

በሀገራችንም ጤና ነክ መረጃዎችን የማጋራት ድርጊት በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ማስተዋል የሚቻል ሲሆን በተለይም በዩቱብና በቲክቶክ በርካታ ቻናሎች ተከፍተው የጤና መረጃን ሲጋሩ፣ ህክምና ሲሰጡ፣ መድሃኒት ሲያዙ እንዲሁም የስነልቦና ምክር ሲሰጡ መመልከት የየዕለት ክንውን ሆኗል። ሳይናስዊ ስነዘዴን እና የሳይንስ ውጤቶች የሆኑ መድሐኒቶችናና የህክማን ዘዴዎችን ማኮሰስም በስፋት ይስተዋላል። እንዲህ ያሉት ቻናሎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር እይታ በእያንዳንዱ ይዘት እንደሚያገኙም በቀላሉ መመልከት ይቻላል።

የጤና ሚንስቴር ጉዳዩ እንዳሳሰበው ከቀናት በፊት የገለጸ ሲሆን ዜጎችም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል። አሳሳችና አደገኛ የጤና መረጃዎች በተለይም በቲክቶክ ጎላ ብለው መታየታቸውን የገለጸው ሚንስቴሩ የድርጊቱ ከዋኞችም ሃላፊነት የጎደላቸው፣ የጤና ሙያ ሳይኖራቸው የጤና ሞያዊ ምክር እንሰጣለን የሚሉ ግለሰቦች መሆናቸውን አስታውቋል።

ከጤና አንጻር የሚሰራጩ አሳሳችና ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው መረጃዎች የሚያደርሱት ጉዳት የከፋ መሆኑን በመገንዘብ በማህበራዊ ሚዲያዎች የምንመለከታቸውን እንዲህ ያሉ መልዕክቶችን ከማመናችንና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል። መረጃውን የሚያሰራጩት ግለሰቦች ተገቢው የህክምና ትምህርትና የሙያ ማረጋገጫ እንዳላቸው መፈተሽ ጠቃሚ ነው።

እንዲሁም የህመም ስሜት ሲሰማን ወደህክምና ተቋም መሄድ ወይም የህክምና ባለሙያን ማማከር ቀዳሚ አማራጭ መሆኑን ማመን ጠቃሚ ነው። ስለህምም ስሜቶች ምንነት የበለጠ ለማወቅ ከፈለግን ደግሞ እንደ በአለም ጤና ድርጅትና ሌሎች እውቅና ወደአተረፉ ድረገጾች ማምራት ይመከራል።

በማህበራዊ ሚዲያ በሚጋሩ አሳሳች እና ሳይንሳዊ መሰረት በሌላው የጤና መረጃዎች ሳቢያ ከሚደርስ የከፋ ጉዳት እራሳችንን እንጠብቅ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::