በማህበራዊ ሚዲያ የሚጋሩ ሀይማኖትና ማንነት ተኮር የጥላቻ መልዕክቶችን ለመቀነስ አስተዋጾ እናድርግ!

ጥላቻ

መስከረም 09፣ 2016 ዓ.ም

የጥላቻ ንግግር በሀገራችን ዘርፈ ብዙ መስቅልቅል ላስከተሉ ግጭቶች እንደ አንድ ገፊ ምክንያት ተደርጎ በብዙዎች ይጠቀሳል። ያደረሰውን ጉዳት የሚተነትኑ የጥናት ውጤቶችም ታትመዋል።

በጥላቻ ንግግር ሳቢያ የቤተሰብ አባሎቻችን ተገድለዋል ያሉ ዜጎችም ጉዳዩን ወደ ፍርድቤቶች ሲወስዱ ተስተውሏል።

ይህም ሆኖ ግን የጥላቻ ንግግር ድርጊት ሲቀንስ ወይም ሲገታ አልተስተዋለም። ይልቁንም ጊዜ እየጠበቀ ማገርሸቱን ቀጥሏል። ይህ ለማስተዋልም የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን መከታተል በቂ ነው።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታትም ሀይማኖት እና የብሔር ማንነት ላይ ትኩረት ያደረጉ የጥላቻ መልዕክቶች ተባብሰው ብቅ ብለዋል። እነዚህ እኩይ መልዕክቶች በተለይም በፌስቡክ፣ በቲክቶክና በኤክስ በቀድሞው ትዊተር በስፋት በመጋራ ላይ ናቸው። ተዋናዮችም በሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያላቸው ሰዎች መሆናቸው ስጋት ያጭራል።

እንዲህ ያሉት አሉታዊ መልዕክቶች መሬት ወርደው በመካሄድ ላይ ያሉ ግጭቶች እንዲባባሱና እንዲራዘሙ ከማድረግ ባለፈ አዳዲስ ግጭቶችን እንዳያጭሩ ያስፈራል።

ስለሆነም ሁሉም ሀላፊነት የሚሰማው ዜጋ የጥላቻ መልዕክቶች ባለፉት ዓመታት ለተፈጠሩ ምስቅልቅሎች ያደረጉትን አሉታዊ አስተዋጾ በመረዳት የበኩሉን አወንታዊ ሚና ሊወጣ ይገባል።

የመጀመሪያው ማድረግ የምችለው አወንታዊ አስተዋጾ የጥላቻ መልዕክት ያላቸውን ይዘቶች በማዘጋጀትና በማሰራጨት ላይ አለመሳተፍ ነው። እንዲሁም የጥላቻ መልዕክት ያላቸውን ይዘቶች የሚያሰራጩ አካላትን አለማበረታትም ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ድርጊት ይሆናል።

ሌላኛው በጉ አስተዋጾ ልናደርግበት የምንችለው መንገድ የጥላቻ መልዕክት ያላቸው ይዘቶችን የሚያሰራጩ አካላትን ማጋለጥና ያጋሩትን ይዘት ሪፖርት ማድረግ ነው። ለዚህም ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርሞች ቀላል የሪፖርት ማድረጊያ ዘዴ እንዳላቸው ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። ይህን ካለመታከትና በተደጋጋሚ ማድረግ ከቻል ድርጊቱን በሚታይ ደረጃ ለመቀንስ እንችላለን።

የጥላቻ ንግ ግር ኢላማ ከሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር መቆምም ሀላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የሚጠበቅ ግዴታ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።

ይህን ካደረግን የጥላቻ መልዕክቶችን ስርጭት በእጅጉ በመቀነስ ለራሳችን፣ ለበቤተሰቦቻችንለማህበረሰባን እና ለሀገራችን የተሻለ ከባቢ መፍጠር እንችላለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::