ካናዳ ልከን ስራ እና ትምህርት እናመቻቻለን የሚሉ አጭበርባሪዎች ጉዳይ

Fraudsters deceive people into believing they can give them jobs and education

የካቲት 11፣ 2016 ዓ.ም

በቅርብ ቀናት በተለይ ቲክቶክ፣ ዩትዩብ እና ቴሌግራም በመጠቀም ካናዳ ልከን ትምህርት እንዲሁም ስራ እናመቻቻለን የሚሉ ግለሰቦች በርካቶችን ገንዘብ እያጭበረበሩ እንደሆነ አንድ ጥቆማ ለኢትዮጵያ ቼክ ደርሶ ነበር።

ይህን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ ቼክ +251907973210 የሆነ የስልክ ቁጥር የሚጠቀም “አብርሀም” የተባለ ግለሰብን አገልግሎት ፈላጊ ሆኖ ቀርቦ አነጋግሯል።

ግለሰቡ ሲያስረዳ ማንኛውም ፓስፖርት ያለው ሰው የፕሮሰስ ማስጀመርያ 3,500 ብር ከከፈለ በኋላ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ብቁ ካደረገ በኋላ ወደ ካናዳ ለትምህርት እና ስራ እንደሚልክ ይናገራል። ሌላው ቀርቶ ለአውሮፕላን ቲኬት የሚሆን ክፍያን ራሱ እንደሚፈፅም፣ በኋላ ስራ ከጀመሩ በኋላ ግን ተገልጋዮች መልሰው እንደሚከፍሉ ያስረዳል።

ግለሰቡ የሚጠቀምበት አንድ በቅንብር የተሰራ ፎርምን የተመለከትን ሲሆን (ምስሉ ተያይዟል) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አርማን እንዲሁም በቤልጅየም፣ ብራሰልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነን ስም እና ፊርማ ያሳያል። ፎርሙ ካናዳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ሀይል እንደምትፈልግ ገልጾ ተመዝጋቢው (ተጭበርባሪው) ግለሰብ ፕሮሰስ ለመጀመር እንዲፈርም ይጠይቃል።

ኢትዮጵያ ቼክ ይህን ዶክመንት ሁለቱም ተቋማት እንደማያውቁት፣ ይልቁንም በቅንብር የተሰራ መሆኑን አረጋግጧል።

አብርሀም የተባለው ግለሰን እጅግ በርካታ ከሆኑ ሰዎች 3,500 ብር እየሰበሰበ እንደሆነም ደርሰንበታል፣ ለዚህ የሚጠቀምበትን የባንክ አካውንትም ደርሰንበታል።

በተጨማሪም ካናዳ የሰው ሀይል ሲያስፈልጋት በመንግስት ተቋሞቿ እና አብራቸው በምትሰራቸው ኤጀንሲዎች በኩል እንጂ በደላሎች ወይም በቲክቶክ እና ቴሌግራም በሚያስተዋውቁ ግለሰቦች እንዳልሆነ የካናዳ ኤምባሲ በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ቼክ አሳውቆ ነበር።

ኤምባሲው በወቅቱ እንዳስረዳን “ህጋዊ በሆነ መልኩ ስራዎቻቸውን ማስተዋወቅ የሚችሉት የተፈቀደላቸው ወኪሎች ብቻ ናቸው” ብሏል።

“ክፍያ ከሚቀበሉ፣ ነገር ግን ካልተፈቀደላቸው ወኪሎች ጋር አንሰራም” ይላል ስለ ወኪሎች የሚያብራራው የኤምባሲው የድረ-ገጽ ክፍል። ወኪሎች የተፈቀደላቸው ናቸው የሚባሉት በካናዳ ባሉ ሶስት የህግ ማህበራት ውስጥ መስፈርቶችን አሟልተው አባል የሆኑ እንደሆነ ብቻ እንደሆነም ያብራራል።

የካናዳ ጉዞዎችን በተመለከተ የበለጠ ለመረዳት ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይከተሉ እና ራስዎን ከአላስፈላጊ ወጪ ይጠብቁ።

https://www.canada.ca/en/immigration-refugees-citizenship/services/immigration-citizenship-representative/learn-about-representatives.html

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::