በግጭት ወቅት አዉድ በሳተ መልኩ ከሚሰራጩ አሳሳች ምስሎች እንጠንቀቅ!

fake image

ሰኔ 01፣ 2015 ዓ.ም

ከሰሞኑ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በተከሰተው ግጭት በሰው ህይወት እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ በስፋት እየተዘገበ ይገኛል።

ጉዳዩ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ዘንድ የመወያያ ነጥብ ከመሆኑም በተጨማሪ በግጭቱ የደረሱ ጉዳቶችን ያሳያሉ የተባሉ ምስሎችም እየተጋሩ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ እይተሰራጩ ባሉ ምስሎች ላይ ባደረገዉ ምርመራ በርካታ ከዚህ በፊት ሌላ ቦታ ጥቅም ላይ የዋሉና ከግጭቱ ስፍራ ያልተወሰዱ ምስሎች አዉዳቸዉን በሳተ መልኩ ሲጋሩ ተመልክቷል።

ለምሳሌ ‘የአማራ ሕዝባዊ ኃይል Official Page!’ የሚል ስም ያለዉ እና ከ8000 በላይ ተከታዮች ያሉት የትዊተር አካዉንት በደብረ ኤልያስ ስላሴ ገዳም መነኮሳት ላይ የተፈጸመ ግድያ የሚያሳይ መሆኑን በመጥቀስ ከአንድ ቀን በፊት ከታች የሚታየዉን ምስል አጋርቷል።

ሰበር ዜና ከሚል የጽሁፍ መረጃ ጋር የቀረበውን ይህን ምስል ከ200 በላይ የትዊተር ተጠቃሚዎች መልሰዉ ያጋሩት ሲሆን በርካታ ግብረመልስም አግኝቷል።

ይሁን እንጂ ምስሉ ከአመታት በፊት በኬንያ ዉስጥ የተነሳ፤ በአልሸባብ ጥቃት ህይወታቸዉ ያለፈ ንጹሀን ዜጎችን አስክሬን የሚያሳይ እንዲሁም የተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎችም ለዘገባዎቻቸዉ ተጠቅመዉበት የነበረ መሆኑን ኢትዮጵያ ቼክ ማረጋገጥ ችሏል።

አዉድ በሳተ መልኩ ከሌላ ቦታ ተወስደዉ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ከማጋለጥ በተጨማሪ ሰዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዳይወስኑ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በተጨማሪም በሰዎች ላይ የስነ-ልቦና ጫና ከማሳደር ባለፈ ለግጭቶች መከሰት እና በሰው እንዲሁም ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሊሆኑም ይችላሉ።

ስለዚህም አጠራጣሪ ምስሎችን ስንመለከት መልሰን ከማጋራታችን በፊት ትክክለኛነታቸዉን በማረጋገጥ ጥንቃቄ እናድርግ።

በሌላ በኩል በደብረ ኤልያስ ወረዳ የተከሰተዉን ግጭት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመጉ ግንቦት 28/2015 ዓ.ም ባወጣዉ መግለጫ በብሄረ ብጹዓን አጼ መልክዓ ስላሴ እና ተክለ ሀይማኖት ገዳማት በአካባቢዉ የታጠቀ ቡድን እየሰለጠነ ነዉ በሚል ምክንያት ከግንቦት 22/2015 ዓ/ም ጀምሮ በነበረ የተኩስ ልውውጥ በንጹሃን ላይ ግድያና የአካል ጉዳት የደረሰ መሆኑን መረጃ ማግኘቱን ገልጿል።

በተጨማሪም ከግንቦት 18/2015 ዓ/ም 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ወደ ገዳማቱ እየተደረገ መሆኑን፤ በዚህም ምክንያት የአካባቢዉ አርሶ አደሮች በሰላም የግብርና ስራቸዉን ለመስራት እንደተቸገሩ እና የገዳማቱ መናኝ መነኩሴዎችም ላይ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን በመግለጫዉ ተካቷል።

በሌላ በኩል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል “በጎጃም ደብረ ኤልያስ ሥላሴ ገዳም መሽገው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ በነበሩት እስክንድር ነጋና ግብረዓበሮቹ ላይ በተወሰደው እርምጃ ክልሉን የማተራመስ ሴራቸው ከሽፏል” ብሏል።

በተጨማሪም “ገዳሙን ከለላ በማድረግ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ በተወሰደው እርምጅ በእስክንድር ነጋና በግብረዓበሮቹ ለውጊያ ሲውል የነበረው ምሽግ መሰበሩንና በ200 ታጣቂዎችም ላይ እርምጃ ተወስዷል” ሲል የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫዉ ገልጿል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::