በአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስም ከተከፈቱ ሀሰተኛ ቲክቶክ አካውንቶች እንጠንቀቅ!

fake tiktok accounts impersonating artist tewodros kassahun teddy afro

ሰኔ 28፣ 2015

የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ስም እና ምስልን በመጠቀም የተከፈቱ የቲክቶክ አካውንቶች ሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ተመልክተናል።

በአርቲስቱ ስም የተከፈቱ በርከት ያሉ አካውንቶች ፖለቲካዊ እና ሀይማኖታዊን ጨምሮ የተለያዩ ይዘቶች ያሏቸውን ቪድዮዎችን የሚያጋሩ ሲሆን በርካታ ተከታዮች እና ተመልካቾችን ማካበት ችለዋል።

ከነዚህ መካከል ‘ቴዎድሮስ ካሣሁን(ቴዲ አፍሮ)✅’ የሚል ስምና ከ71 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የቲክቶክ አካውንት የገንዘብ ድጋፍን የሚጠይቁ ቪዲዮዎችን እያጋራ ይገኛል።

ይህ አካውንት የተለያዩ ግለሰቦችን ምስል በሚያጋራቸው ቪዲዮዎች በማካተት ግለሰቦቹ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና ሰዎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል።

ለምሳሌ ያክልም በዚህ አካውንት ከተጋሩ ቪድዮዎች መካከል በአንዱ የአንድ ታዳጊ ተንቀሳቃሽ ምስል የሚታይ ሲሆን “እኔ ያቅሜን 150,000 ብር አስገብቻለሁ ለባጃጅ መግዣ” የሚል ጽሁፍ ይነበባል፤ ሌሎች ሰዎችም ለታዳጊው ድጋፍ እንዲያደርጉ ይጠይቃል።

ገንዘብ ገቢ የሚደረግበት የባንክ ሂሳብ ቁጥርም በቪዲዮዎቹ የተካተተ ሲሆን ለተለያዩ ሰዎች በተመሳሳይ አካውንት ገንዘብ ገቢ እንዲደረግም ይጠይቃል። ይህ በራሱ ጥርጣሬን ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ቢሆንም እንኳ ቪድዮዎቹ የበርካታ ቲክቶክ ተጠቃሚዎችን መዉደድ (like) አግኝተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ‘teddy afro’ በሚል በአርቲስቱ ስም የተከፈተ የቲክቶክ አካዉንት 142 ሺህ ተከታዮች እና ከ1.5 ሚልዮን በላይ መዉደድ (like) እንዳለው ማየት ችለናል።

እነዚህ እና ሌሎች በአርቲስቱ ስም የተከፈቱ አካውንቶችን ትክክለኛነት በተመለከተ ኢትዮጵያ ቼክ የአርቲስት ቴዲ እፍሮን ማናጀር ጌታቸው ማንጉዳይ ያናገረ ሲሆን አርቲስቱ የቲክቶክ አካውንት እንደሌለው ነግረዉናል።

በአርቲስቱ ስም በተከፈተ የቲክቶክ አካውንት የሚቀርበውን የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄን በተመለከተም “የምናዉቀው ጉዳይ የለም። ዉሸት ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

የታዋቂ ተቋማት፤ አርቲስቶች፤ የመንግስት ሃላፊዎችና ፖለቲክኞችን ስም እና ምስል በመጠቀም የሚከፈቱ ሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር አካውንቶችና ገጾች ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የተሳሳተ ግንዛቤን ሲፈጥሩ ማየት የተለመደ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።

ስለዚህም ትክክለኛና የተረጋገጡ የማህበራዊ ትስስር አካውንቶች፤ ገጾች እና ቻናሎችን ብቻ በመከተል ለሀሰተኛና አሳሳች መረጃዎች እንዳንጋለጥ ጥንቃቄ እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::