ይህ ቪዲዮ በጎንደር የተከሰተን የእሳት ቃጠሎ አያሳይም!

gondar

መስከረም 16፣ 2016 ዓ.ም

ከ101,800 በላይ ተከታዮች ያሉትና ‘ETH tiktok’ መጠሪያ የሚጠቀም የቲክቶክ አካውንት “ጎንደር ነደደች” በሚል ርዕስ ስር ቪዲዮ ማጋራቱን ተመልክተናል። በቪዲዮው የሚቃጠል ተራራማ አካባቢና ሂሊኮፕተር ይታያሉ።

አካውንቱ ይህን ቪዲዮ ሌሎች መልሰው እንዲያጋሩት የሚያበረታታ መልዕክትም የጻፈ ሲሆን ከ5,700 በላይ ሰዎችም መልሰው ማጋራታቸውን አስተውለናል።  ሌሎች በርካታ የቲክቶክ አካውንቶችም ቪዲዮውን በተለያየ መልኩ አጋርተውታል።

ምንም እንኳን ባለፉት ቀናት በጎንደርና አካባቢያዋ ግጭት ተከስቶ እንደነበር የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትና የጎንደር ከተማ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ባወጧቸው መግለጫዎች መግለጻቸው እንዲሁም አለም አቀፍ ሚዲያዎች መዘገባቸው የሚታወቅ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሰው የቲክቶክ አካውንት ያጋራው ቪዲዮ ግን ጎንደርና አካባቢዋን እንደማያሳይ ኢትዮጵያ ቼክ አረጋግጧል።

ቪዲዮው በኒውዝላንድ አገር የተቀረጸ ሲሆን ያጋራውም ዌይ ቱ ጎ ሄሊሰርቪስ (Way TO Go Heliservices) የተባለ የሄሊኮፕተር አገልግሎቶችን የሚሰጥ ኩባንያ ነው።

በቪዲዮው ላይ የሚታየውም የኩባንያው ንብረት የሆነ ሄሊኮፕተር የማይፈለጉ እጽዋቶችን ሲያቃጥል መሆኑን ዌይ ቶ ጎ ሄሊሰርቪስ በቲክቶክና በፌቡክ ገጾቹ መግለጹን ተመልክተናል። ትክክለኛን ቪዲዮ ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ማግኘት ይችላሉ: https://fb.watch/njJZBIyEdC/?mibextid=Nif5oz

በተመሳሳይም በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ከአውድ ውጭ እየቀረቡ ያሉ ምስሎች፣ ቪዲዮዎች እና የጽሁፍ መረጃዎች እንዳሉ መመልከተ የቻል ሲሆን እነዚህን አሳሳች መረጃዎች ባለማጋራት የራሳችንን አስተዋጾ እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::