መረጃን ማጣራት እና ተግዳሮቶቹ!

twitter verification

ሰኔ 12፣ 2015

ባለፉት ጥቂት አመታት በመላው አለም የታየው የሀሠተኛ መረጃ ስርጭት መስፋፋት እና የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ጉዳት የመረጃ ማንጠር ሙያ እና የመረጃ አንጣሪ ተቋማት በመረጃ ገብያው ውስጥ ዋነኛ ተዋንያን ሆነው ብቅ እንዲሉ አድርጓል። የመረጃ ማንጠር ሙያተኞች እና ተቋማት የሀሠተኛ መረጃ ስርጭትን በመዋጋት የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ ቢሆንም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው በርከት ያሉ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል።

መረጃ አንጣሪዎች ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ መረጃን በማጣራት ሂደት ውስጥ ቁልፍ የሆነውን የማመሳከሪያ እውነት (fact) በተደራጀና በተገቢው ሰዐት አለማግኘት ነው። ይህ ተግዳሮት በተለይም መረጃን በተገቢው መንገድ አደራጅቶ በግለጽ ለተጠቃሚዎች የማድረስ ባህል ባልተለመደበቸው ሀገራት ጎላ ብሎ ይታያል።

ገልለተኛ እና ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን እና ተንታኞችን አለማግኘት ሌላው መረጃ አንጣሪዎችን የሚገጥማቸው ፈተና ነው። በተለይም የፖለቲካ መስተጋብሩ ዋልታ ረገጥ በሆነባቸው የፖለቲካ ማህበረሰቦች ውስጥ ገለልተኛ ባለሙያና ተንታኝ ማግኘትና ገለልተኝነትን መበይን ዋንነኛ ተግዳሮት መሆኑ ይጠቀሳል።

እንዲሁም ከሚመሳከረው መረጃ አኳያ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግስት እና የግል ተቋማት ሀላፊዎች፣ የአይን ምስክሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን መረጃ አንጣሪዎች በየዕለት የስራ ክንውናቸው የሚገጥማቸው ተግዳሮት ነው።

መረጃ አንጣሪዎችን ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች ሌላኛው መረጃን በማንጠር ሂደት ውስጥ የማይተካ ሚና የሚወጡ መተግበሪይና መገልገያ የቴክኖሎጅ ውጤቶችን (fact-checking tools) አለማግኘት ነው። በተለይም ይህ ተግዳሮት በቴክኖሎጅ ወደኃላ በቀሩ ሀገራት በሚገኙ የመረጃ አንጣሪ ተቋማት በስፋት ይታያል።

ዝግ በሆኑ እንደ ዋትስአፕ፣ ሲግናል እና ቴሌግራም በመሳሰሉ የግንኙነት አውታሮች በከፍተኛ ሁኔታ የሀሰተኛ መረጃ ቅብብሎሽ መኖሩ እውነት ቢሆንም ይህን ዝግ ቅብብሎሽ ለመከታተል እና የግለሰቦችን ነጻነት ሳይጋፉ መረጃ ለማጣራት አለመምቻል ሌላው መረጃ አንጣሪዎች የሚገጥማቸው ተግዳሮችት ነው።

ከግጭት አገናዛቢነት አኳያ የሚከሰት ግለ-ሳንሱር ሌላኛው መረጃ አንጣሪዎችን የሚገጥማቸው ተግዳሮት ነው። ግጭት እና የፖለቲካ መካረር በሚታይበት የፖለቲካ ከባቢ የሚሰሩ መረጃ አጣሪዎች እውነታን ገሃድ በማውጣት እና ግጭትን ባለማባባስ መካከል ግለ-ሳንሱር ሲከውኑ ይስተዋላል። እንዲህ አይነቱ ሳንሱር የሰዎችን ህይዎት እስከመታደግ የሚደርስ ግጭት አገናዛቢነት ቢሆንም እንደ ገለልተኝነት ያሉ የመረጃ ማንጠር ሙያ መርሆች ጋር ይጣረሳል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::