እነዚህ ምስሎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሊገነባው ያቀደውን የኤርፖርት ከተማ ንድፍ አያሳዩም

ታህሳስ 03፣ 2016 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ ቢሾፍቱ አከባቢ ሊገነባ ያሰበውን ‘ኤርፖርት ሲቲ’ የተመለከቱ ዜናዎች መሰራጨታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋሩ ይገኛሉ።

በርከት ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎችም የስክሪን ቅጂያቸው የሚታየውን ምስሎች አየር መንገዱ ሊገነባ ያቀደውን ‘ኤርፖርት ሲቲ’ የሚያሳይ ንድፍ መሆኑን በሚገልጽ መልኩ ሲያጋሩ ተመልክተናል።

ሌሎች ደግሞ ከሌላ ድረ-ገጾች ወይም ሌላ ምንጮች የተወሰዱ መሆናቸውን ሳይገልጹ ምስሎቹን ከመረጃው ጋር እያጋሩ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ የኤርፖርት ሲቲ ግንባታው እቅድ የተመለከተው መረጃ ትክክለኛ ቢሆንም ምንጭ ሳይጠቀስ ከአውድ ውጭ እየተጋሩ የሚገኙት ምስሎች ግን አሳሳች መሆናቸውን ተመልክተናል።

እነዚህ በስፋት እየተጋሩ ከሚገኙ ምስሎች መካከል አንደኛው ውድስ ባገት (Woods Bagot) የተሰኘ የአርክቴክቸር ተቋም ለቻይና ሳውዘርን ኤርላይንስ ከ10 ዓመታት በፊት የሰራው የኤርፖርት ከተማ ንድፍ /ዲዛይን/ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የደቡብ ኮሪያው ግዙፉ ኢንሸን ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ንድፍ ነው።

የነዚህን ሁለት ኤርፖርቶች ንድፍ በነዚህ መስፈንጠሪያዎች መመልከት ይቻላል፡

https://www.architectmagazine.com/project-gallery/china-southern-airport-city

እና https://www.koreaherald.com/view.php?ud=20191119000078

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‘በአፍሪካ ትልቁ አየር ማረፊያ’ የተባለውን ‘ኤርፖርት ሲቲ’ ግንባታ እቅድ ይፋ ካደረገ ሰነበብቷል፡ https://ethiopianairlines.ca/2020/02/05/ethiopian-airlines-announces-plans-to-build-africas-largest-airport/

የዛሬ አመት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በድረ-ገጹ ባጋራው ዜና ተቋሙ ‘የኤርፖርት ሲቲ’ ግንባታዉን በ2015 በጀት አመት ለመጀመር የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የድርጅቱን ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር፡ https://www.ena.et/web/amh/w/am_197074

ሰሞኑንም አየር መንገዱ ግንባታውን ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ እየተዘገበ ይገኛል፡ https://waltainfo.com/am/%e1%8a%a0%e1%8b%a8%e1%88%ad-%e1%88%98%e1%8a%95%e1%8c%88%e1%8b%b1-%e1%8b%a8%e1%8a%a4%e1%88%ad%e1%8d%96%e1%88%ad%e1%89%b5-%e1%88%b2%e1%89%b2-%e1%8c%8d%e1%8a%95%e1%89%a3%e1%89%b3-%e1%89%a0%e1%8a%a0/

ትክክለኛ ለሆኑ መረጃዎች አሳሳች ምስሎችን መጠቀም ለተዛባ መረጃ ስለሚያጋልጥ ጥንቃቄ እናድርግ።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::