በአርትዖት ቃላትን በመቀየር በማህበራዊ ሚድያ የተጋራ የተዛባ ቅጅ!

በዐርትዖ ቃላትን በመቀየር በማህበራዊ ሚድያ የተጋራ የተዛባ ቅጅ!

ህዳር 22፣ 2016

ሪፖርተር ጋዜጣ በህዳር16/2016 ዓ.ም ዕትሙ የፊት ገጽ ላይ “በወረራ የተያዘውን የኢትዮጵያ መሬት በድርድር ለማስመለስ የሱዳንን ሰላም መሆን እየጠበቀ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ” የሚል ርዕስ ያለው መረጃ ይዞ ወጥቶ ነበር። ጋዜጣው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የ2016 ዓ.ም የሦስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በመረጃ ምንጭነት መጠቀሙን ገልጿል።

ሪፖርቱ በቀረበበት ዕለት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰንበትን አልፋሽጋ ድንበር በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ፍሰሐ ሻውል (አምባሳደር) “ኢትዮጵያ ከድንበር ባሻገር ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት እጅግ ታሪካዊና በርካታ ጉዳዮችን የሚያካች በመሆኑ፣ ያንን ግምት ውስጥ በማስገባት ሱዳን ከችግር በምትላቀቅበት ጊዜ በድርድር እንጨርሰዋለን” ብለው ስለመናገራቸውም ጋዜጣው ጠቅሷል። የጋዜጣውን ሙሉ ዘገባ ይህን ማስፈንጠሪያ በመከተል ማግኘት ይቻላል: https://www.ethiopianreporter.com/124338/

ሆኖም ከሰሞኑ ይህን የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ የሚያዛባ የአርትዖት ስራ የተከወነበት ቅጅ በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ተመልክተናል።

የአርትዖት ስራ የተከወነበት ቅጅ በዜናው ርዕስ ላይ የሚነበበውን “በድርድር” የሚለውን ቃል “በፀሎት” በሚል ቃል በመተካት “በወረራ የተያዘውን የኢትዮጵያ መሬት በፀሎት ለማስመለስ የሱዳንን ሰላም መሆን እየጠበቀ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ” የሚል የተዛባ ትርጉም እንዲሰጥ አድርጓል።

የአርትዖት ስራው በተመሳሳይ የፊደላት ቅርጽ፣ ድምቀትና መጠን በመሰራቱም አንዳድ ሰዎች እውነት እንደመሰላቸውን ተመልክተናል።

እንዲህ ያሉ ቀላል የሚመስሉ፣ ምናልባትም ለቀልድና ለማሾፍ ተብለው የሚሰሩ የአርትዖት  ስራዎች መረጃዎችን ሊያዛቡና ሰዎችን ሊያሳስቱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::