በማህበራዊ ሚዲያ በሚጋሩ ይዘቶች ስር የሚጻፉ አስተያየቶችን ማንበብ እውነተኛ መረጃን ለማግኘት የሚኖረው አስተዋጾ!

ጷጉሜ 01፣ 2015 ዓ.ም

በማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ከምናያቸው መረጃዎች መካከል አንዳንዶቹ እውነተኛ ስለመሆናቸው ጥርጣሬ ውስጥ ይከቱንና ቆም ብለን እንድናስብ ያደርጉናል። እውነታውን ለማወቅም ፍላጎት ያድርብናል። ለዚህም ብዙ ቦታ እናማትራለን። የመረጃ አጣሪ እና የሚዲያ ተቋማትን ገጾች እናስሳለን፤ የምልሰት መፈለጊያ መገልገያዎችን እና ሌሎች አጋዥ ቴክኖሎጅዎችን እንሞክራለን፤ ወዳጆቻችን እና የምናውቃቸውን ሰዎች እንጠይቃለን። እንዲህ ያለው ጥረታችን ብዙ ጊዜ ወደ እውነተኛው መረጃ ያደርሰናል። እርቀን መጓዛችንም ሀቁን ከተዛባው እንድንለይ ያስችለናል።

አልፎ አልፎ ግን ብዙ ርቀት መጓዝ ሳያስፈልገን እወንታውን ከተጋራው ይዘት ግርጌ ከተሰጡ አስተያየቶች (commenets) ልናገኘው እንችላለን። በተለይም የተጋራው ይዘት ጥርጣሬ የሚያጭር፣ ስሜታዊ የሚያደርግ፣ የብዙዎችን ትኩረት የሚስብ አይነት ከሆነ ከግርጌ የተሰጡ አስተያየቶችን ማንበብ እውነታውን ለማወቅ በእጅጉ ይረዳል።

ከይዘቶች ግርጌ ከሚሰጡ አስተያየቶች መካከል የተጋራውን መረጃ ሀሠተኝነት በማስረጃ አስደግፈው የሚሞግቱ፤ በተጋራው መረጃ አኳያ ወይም አንጻር አውድ (context) የሚጨምሩ፤ የተጋራው ምስል የቆየ ወይም ከሌላ ቦታ የተወሰደ መሆኑን የሚያጋልጡ፤ ወደ እውነተኛው መረጃ የሚያደርሱ ማስፈንጠሪያዎችን (links) የሚያጋሩ፤ ይዘቱን ያጋራው አካውንት ተመሳስሎ የተከፈተ መሆኑን የሚመሰክሩ ሰዎችን የማግኘት እድል ይኖረናል።

አስተያየት ከሚሰጡ ሰዎች መካከል የድርጊቱ ተሳታፊዎች፣ ድርጊቱ ከተፈጸመበት አካባቢ የሚኖሩ፣ ለድርጊቱ ተሳታፊዎች ቅርበት ያላቸው እንዲሁም ስለጉዳዩ ሙያ ያላቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ሁሌም ማሰብና መገመት ይኖርብናል። አልፎ አልፎ ደግሞ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሰዎች የሰጡትን ምላሽ የማየት አጋጣሚም ይኖረናል።

ስለሆነም በፌስቡክ፣ በዩቱብ፣ በቲክቶክ፣ በቴሌግራም፣ በኤክስ ትዊተር እና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚጋሩ ይዘቶች ስር የሚጻፉ አስተያየቶችን ማንበብ እውነተኛ መረጃ የማግኘት ጥረታችንን ሊያግዝ ስለሚችል ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። በተጨማሪም ተሳታፊ በመሆን ሀሠተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በማጋለጥ፣ አውድ በመጨመር፣ የጥላቻ መልዕክቶችን ሪፖርት በማድረግ አዎንታዊ አስተዋጾ ማበርከት እንችላለን።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::