ኮይንኤምቪ (coinmv) የማጭበርበርያ ድረ-ገፅ ወይስ ትክክለኛ ቢዝነስ?

ኮይንኤምቪ

መጋቢት 24፣ 2015 ዓ.ም

የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያደጉ መጥተዋል፣ ለዚህም ክሪፕቶከረንሲዎች ትልቅ እገዛ እያደረጉላቸው ይገኛሉ።

ከቅርብ አመታት ወዲህ የክሪፕቶ ምንዛሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተወዳጅ እየሆነ መጥቷል፣ ከዚህ ጎን ለጎን ከክሪፕቶ ጋር የተያያዙ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ቁጥርም እየጨመረ መጥቷል።

የአሜሪካው የወንጀል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ በቅርቡ ይፋ ባደረገው አመታዊ የኢንተርኔት ወንጀል ሪፖርት በ2022 በኦንላይን በተፈጸሙ የማጭበርበር ተግባራት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መጥፋቱን አስታውቋል።

ይህ እ.ኤ.አ በ2021 ከነበረው የ6.9 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ በ46 ፐርሰንት ጨምሯል። ይህም ካለፉት አምስት አመታት ውስጥ ከፍተኛው አመታዊ ኪሳራ መሆኑን የቢሮው ዘገባ አመልክቷል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የግብጽ ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሃብቶች ላይ የኢንተርኔት ክሪፕቶ ማጭበርበር ፈጽመዋል ያሉዋቸውን 13 የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 29 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ተዘግቧል።

ይህ “ሆግፑል” የተባለ በነሀሴ ወር የተመዘገበ ሲሆን ደንበኞቹ “በማጭበርበር ካጠመዷቸው በኋላ የገንዘብ ጥቅማጥቅሞች” እንደሚያገኙ ቃል ገብቶላቸዋል ነበር ሲሉ የአገሪቷ አቃቤ ህግ ገልጿል። ይህ ድረ ገጽ “ከክሪፕቶከረንሲ ማይኒንግ እና የንግድ አገልግሎቶች ትልቅ ትርፎች” የሚል ቃል ገብቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ቼክ ተከታታዮች ከክሪፕቶከረንሲ ጋር የተያያዙ እና ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ያደረጉ ድርጅቶችን እንድናጣራላቸው ይጠይቃሉ። ከእነዚህ አንዱ እ.ኤ.አ በ2013 እንደተቋቋማ የሚገልጸው ‘ኮይንኤምቪ’ (coinmv) የተሰኘ ድርጅት ነው።

“የድርጅቱ ህይወት ታሪክ” በሚል ሥር የሰፈረ የስልክ ወይም የኢሜይል አድራሻ ባለመኖሩ ድርጅቱን በቀጥታ ማግኘት አልተቻለም። በድረ-ገጹ ባያያዘው “የንግድ ፍቃድ” ግን ድርጅቱ በአሜሪካ በኮሎራዶ ግዛት የተመዘገበ መሆኑን ያሳያል።

ይህ “የንግድ ፍቃድ” ግን ከቀናት በፊት የተቀመጠ መሆኑን የተመለከትን ሲሆን የተለያዩ የቃላት ግድፈቶችም ይታዩበታል፣ ይህም ድርጅቱን አጠራጣሪ እንዲሆን አድርጎታል።

ጉግል ስለ ድርጅቱ ከሚሰጠን አምስት ቀዳሚ ውጤቶች “ሲኤምቪኮይን – ህጋዊ ወይስ ማጭበርበሪያ (legit or scam)? የሚሉ ናቸው።

አንድን ድረ-ገጽ ትክክለኛ ወይም ማጭበርበሪያ መሆኑን ለማረጋገጥ የምንጠቀምባቸው ‘ስካምአድቫይዘር’ እና ‘ስካም ዲቴክተር’ ደግሞ ስለ ድርጅቱ ያቀረቡት ትንተና እንመልከት።

ስካምአድቫይዘር የኮምፒዩተር ትንተናውን በመጠቀም በሰጠው ብያኔ የድርጅቱ ትክክለኛ SSL ሰርተፊኬት (Secure Sockets Layer) ማግኘቱን እና ድረገጹ ለበርካታ አመታት የቆየ መሆኑን ይገልጻል። ይሁን እንጂ አንድን ድርጅት መቼ ተመዘገበ የሚለውን በሚያሳውቀው ‘WHO-IS’ የባለቤቱን ማንነት ድብቅ መሆኑ፣ ለዚህ ድረ-ገጽ አሉታዊ ግምገማዎች መገኘታቸው እና ገጹ ይዘቱን እንድንመረምር አይፈቅድልንም ይላል።

ስካም ዲቴክተር በበኩሉ የድርጅቱ ዶሜይን በ2017 እንደተከፈተ በመግለጽ የድረ-ገጹ ሪከርድ ደካማ መሆኑን እና ለሚያጠራጥሩ ድረገጾች የሚጠጋበት እድል 45 ፐርሰንት ነው ይላል። አክሎም www.coinmv.com ከታዋቂው የክሪፕቶ ኤክስቼንጅ ኒቼ ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ መጠን ይህ ድረ-ገጽ በደካማ ሁኔታ የተሰራ በመሆኑ ታማኝነቱን እንዲያጣ እና ጥራቱ ለጊዜው አጠራጣሪ መሆኑን ያሳያል። ይህን እንዳሻሻሉ መረጃውን እናሻሽለዋለን” ይላል።

የዚህ ድርጅትን ድረ-ገጽ እንዲመረምሩ ኢትዮጵያ ቼክ ያነጋገራቸው የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች በበኩላቸው፡ ዌብሳይቱ በትክክለኛ መንገድ የተመዘገበ ቢሆንም ‘የኮይን’ ቢዝነሳቸው ‘ስካም’ መሆኑ ያሳያል የሚል ግምት አላቸው።

“ማጭበርበሪያ የመሆን ከፍተኛ እድል አለው” የሚለው የክሪፕቶከረንሲ ባለሙያ የሆነውን አብነት ተፈራ ከዚህ ጋር መነሳት የሚችሉ በርካታ አደጋዎች አሉ በማለት ይዘረዝራል።

አንድ፡ የሚገበያዩ ሰዎች በየቀኑ ንቁ ተጠቃሚዎች ባሉበት ልውውጥ እንዲጠቀሙ መፈለጋቸው ሲሆን ተጠቃሚዎቹ የግል ቁልፎች ወይም የልውውጡ ዋና ቁልፍ ባለቤት አለመሆናቸው ደግሞ ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ያስረዳል።

ይህ ማለት በሌላኛው ጥግ ያሉ ግብይቱን የሚከታተሉ የድርጅቱ ሰዎች የተጠቃሚው ክሪፕቶ ማየት እና ክሪፕቶውን በጓሮ በር በኩል ማግኘት እና ማውጣት ይችላሉ (ለምሳሌ የካናዳው የFTX ልውውጥ የሆነው ‘Quadriga’ 190 ሚሊዮን ዶላር የካናዳ ተጠቃሚዎች ይዞ እንደጠፋው)።

በሌላም በኩል ህጋዊ ቢሆኑም በማንኛውም ጊዜ ሊያጭበረብሩ እና ገንዘባቹን ይዘው መጥፋት እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ። ከዚህ ባሻገር ያልታወቁ ልውውጦች በደህንነት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃዎች የላቸውም።

“ይህ ድርጅት ደግሞ ህጋዊ ቢሆንም፤ የገንዘብ ልውውጡ፣ የገበያው ጥልቀት፣ ስርጭት እና የመግዛትና የመሸጫ ክፍያዎቹ አይታወቁም። ከየትኛውም የቁጥጥር ባለስልጣን የመስራት ፍቃድ እንዳላቸው አናውቅም፤ የደንበኛ ድጋፍ (custom support) እንዳላቸው እንኳን አናውቅም” ይላል አብነት።

ክሪፕቶከረንሲ በአጭር ቋንቋ የማይዳሰስ የዲጂታል ገንዘብ ማለት ነው። ይህ የገንዘብ ልውውጦችን ደኀንነት የሚያረጋግጥ፣ የተጨማሪ አሃዶች መፈጠርን የሚቆጣጠር እና ገንዘብ መተላለፉን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ‘ክሪፕቶግራፊ’ የሚጠቀም መገበያያ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ ዲጂታል ገንዘብ ነው።

በየቀኑ ንቁ ተጠቃሚዎች ባሉበት መገበያየት እና ለመግዛት አጠቃላይ የክሪፕቶ ህግ መሆኑን የሚገልጸው አብነት ምናልባት የመረጃ ጥሰት እንዳይከሰት ተጠቃሚው ደህንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ርዝመት ያላቸው የደህንነት እርምጃዎች ባሉበት ልውውጥ እንገበያያለን ሲል ያስረዳል።

እንደ ባይናንስ (Binance)፣ ክራከን (Kraken)፣ ቢንግ ኤክስ (Bing X)፣ ባይቢት (Bybit)፣ ዴልታ (Delta)፣ ኮይንቤዝ (Coinbase)፣ ኦኬኢኤክስ (OkEx)፣ ቢትሜክስ (Bitmex)፣ ጌት ኣይኦ (gate io)፣ ዊቡል (WeBull) ህጋዊ ናቸው ሲል ጠቅሷል።

ሰዎች በብዛት ባይናንስ እና ቢንግ ኤክስ የሚጠቀሙ ሲሆን ባይቢት ተመራጭ የክሪፕቶ ግብይት መሆኑ አብነት ይናገራል። ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ግን Binance፣ Bing X እና Bybit እንዲጠቀሙ ይመክራል።

ጥቂት አገራት ቢትኮይንን ሕጋዊ መገበያያ አድርገዋል። በተቀሩት አገራት በተለይ ደግሞ በምዕራባውያን አገራት ህጋዊ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። እንደ ቦሊቪያ፣ ቻይና፣ ኢራን እና ኮሎምቢያ ያሉ አገራት ግን ቢትኮይን ላይ ክልከላ ጥለዋል፣ ወይም ሕገወጥ አድርገውታል።

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::