ራያ ቆቦ አካባቢ እየተደረገ ያለ ውጊያ ያሳያል በሚል የተሰራጩት ምስሎች የቆዩ ናቸው

ሚያዝያ 7፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- በርከት ያሉ የፌስቡክ ገፆች እና አካውንቶች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው ቆቦ ከተማ ውስጥ እና ዙሪያዋ እየተደረገ ነው የተባለ ውጊያን ያሳያል በሚል በምስሎች የተደገፈ መረጃዎች እያጋሩ ይገኛሉ።
አካውንቶቹና እና ገፆቹ መረጃዎቹን በሰበር ዜና መልክ እያሰራጩ የሚገኙ ሲሆን በተለይ ውጊያዎች ላይ ይታያሉ የተባሉ መድፎች ናቸው በሚል በርካታ ምስሎችን እያጋሩ ይገኛሉ።
እነዚህን በፅሁፎች እና በምስሎች የተደገፉ መረጃዎች ካጋሩ ገፆች መካከል ‘ስበር ሻምበል ዳርገ’ የሚል ስም ያለው ከ14 ሺ በላይ ተከታዮች ያለው ገፅ ይገኝበታል።
ገፁ በቆቦ እና በአቅራቢያው በደቡባዊ ትግራይ ዞን በምትገኘው አላማጣ ዙሪያ እየተደረገ ነው ባለው ውጊያ መረጃ ላይ የመድፍ ምስሎች ለጥፎ አስፍሯል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ የጉግልን ምስል በምልሰት መፈለጊያ (Google Lens) በመጠቀም ባደረገው ማጣራት ምስሎቹ የቅርብ ግዜ ሳይሆኑ ከ1990 እስከ1992 ዓ/ም በኢትዮጵያ-ኤርትራ ጦርነት ግዜ የተነሱ ምስሎች መሆናቸውን አረጋግጧል። http://news.bbc.co.uk/2/hi/africa/772434.stm
በተመሳሳይ ‘Raya Press’ በሚል ስም የተከፈተ ከ13,000 በላይ ተከታዮች ያለው የፌስቡክ ገፅ ባጋራው መረጃ ላይ ካሉ ምስሎች አንዱ መድፍ ሲተኮስ የሚያሳይ ምስል ይታያል።
ኢትዮጵያ ቼክ በዚህም ዙርያ የጉግልን ምስል በምልሰት መፈለጊያ (Google Lens) በመጠቀም ባደረገው ማጣራት የመድፉ ምስል የቅርብ ግዜ ሳይሆን ቆየት ያለ ምስል መሆኑን አረጋግጧል።
ከሌላ ቦታዎች ተወስደው ከአውድ ውጭ በሆኑ መልክ የሚጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ማጋራታችን በፊት ተገቢው ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





