በረቀቀ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቅንብር ተሰርቶ ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተጋራ የሚገኘው ቪዲዮ ምንነት

ሰኔ 1፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- አንድ የፋኖ አባል ለመንግስት እጅ እንደሰጠ የሚጠቁም የጽሁፍ እና የቪዲዮ መረጃ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋራ ይገኛል። ይህ የተሰራጨው የጽሁፍ መረጃ “የዘመነ ካሴ አብሮ አደግ እና የዘመነ ካሴ ቀኝ እጅ ቴዎድሮስ የደሜ የሚመራውን ታጣቂ አሰልፎ ወደ ሰላም መጥቷል” የሚል መልዕክት ያዘለ ነው።
በተጨማሪም በቪዲዮው ላይ የሚታየዉ ግለሰብ “እኔና ጓደኞቼ ከመንግስት ጋር በመስማማት እጃችንን የሰጠን ሲሆን ከሻብያ ተላላኪዉ ዘመነ ካሴ ጋር የነበረን ግንኙነት በዚ አብቅቷል” ሲል በግልጽ ይደመጣል።
ይህን የጽሁፍ እና የቪዲዮ መረጃ በስፋት ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ‘የፍቅር መንገድ’ እና ‘ዲጂታል ኢትዮጵያ’ የሚባሉ የፌስቡክ ገጾች በዋነኝነት ይገኙበታል።
በተለይም ‘የፍቅር መንገድ’ በተሰኘዉ ገጽ የተጋራዉን ይኸንን የጽሁፍ እና የቪዲዮ መረጃ ከመቶ አርባ በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰው ለሌሎች ያጋሩት ሲሆን በርካታ አስተያየቶችም ተሰጥተዉበታል።
ይህንን ጉዳይ ተከትሎ ኢትዮጵያ ቼክ መረጃውን ለማረጋገጥ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ ቪዲዮው ፈጽሞ እውነተኛ እንዳልሆነ አረጋግጧል።
ኢትዮጵያ ቼክ የጉግል ምርት የሆነዉን ‘ሲንዝ አይዲ ዲቴክተር’ (SynthID Detector) የተባለውን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ በመጠቀም በቪዲዮው ላይ ባደረገዉ ማጣራት የተሰራጨው ምስል ትክክለኛ ሰውን እንደማያሳይ ደርሶበታል።
በዚሁ የምርመራ ውጤት መሰረት በቪዲዮው ውስጥ የሚታየው ምስልም ሆነ የሚሰማው ድምጽ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ የተቀነባበረ የፈጠራ ውጤት መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።
በቪዲዮው ላይ የሚታየው የከንፈር እንቅስቃሴ፣ የፊት ገጽታ እና የድምጽ ቅንብር አንድን ትክክለኛ ሰው አስመስሎ በኮምፒውተር ፕሮግራም የተሰራ እንጂ በገሃዱ ዓለም የተፈጠረን ክስተት የሚያንጸባርቅ አይደለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚፈበረኩ መሰል የዲፕፌክ (Deepfake) ቪዲዮዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ በጣም እየተበራከቱ እና በርካታ ሰዎችን ለተሳሳተ መረጃ እያጋለጡ ይገኛሉ።
አጥፊ እና አሳሳች መረጃ አሰራጪ አካላት እነዚህን እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም እውነተኛ የሚመስሉ ነገር ግን ፈጽሞ ያልተፈጠሩ ክስተቶችን በመፍጠር ህብረተሰቡን በማሳሳት ላይ ይገኛሉ።
ይህ አይነቱ ቴክኖሎጂ የፖለቲካ ውዥንብር ለመፍጠር፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማራመድ፣ እና የሰዎችን ስነልቦና ለመጉዳት ሆን ተብሎ የሚሰራጭ አደገኛ የሀሰተኛ መረጃ (Disinformation) መሳሪያ ሆኗል።
በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት የፖለቲካ እና የጸጥታ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ግለሰቦች ያልተናገሩትን እንደተናገሩ አድርጎ በማቅረብ ህብረተሰቡ የተዛባ መረጃን አምኖ እንዲቀበል ማድረግ የተለመደ የማጭበርበር ስልት ሆኖ ብቅ ብሏል።
ሰዎች እውነተኛ ቪዲዮ እየተመለከቱ እንደሆነ በማሰብ እንዲታለሉ እና የተዛባ መረጃን ለሌሎች በማጋራት በማህበረሰቡ ውስጥ አለመተማመንን መፍጠር የዚህ አይነቱ ተግባር ዋና አላማ ነው።
ስለሆነም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ይህንን እያደገ የመጣውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት አደጋ በሚገባ ተገንዝበው ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንመክራለን።
ማንኛውም አጠራጣሪ እና ተአማኒ ባልሆኑ የመረጃ ምንጮች ወይም ግለሰቦች የሚጋሩ የምስል እና የቪዲዮ መረጃዎችን ልክ እንዳዩት ከማመናችን እና መልሰን ለሌሎች ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት ማድረግ አለብን።
ቪዲዮዎች ያልተለመደ የዓይን ብልጭታ፣ ከድምጽ ጋር የማይሄድ የከንፈር እንቅስቃሴ ወይም ኢተፈጥሮአዊ የሆነ የቆዳ ገጽታ ካላቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ በጥሞና መመርመር ያስፈልጋል።
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





