በጮቄ ሰንሰላታማ ተራራ የተማረኩ ጦር መሳሪያዎች በሚል በሰበር መልኩ እየተጋሩ ያሉ ምስሎች በሰው-ሰራሽ አስተውሎት የተፈበረኩ ናቸው

ሀምሌ 13፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- ‘በጮቄ ሰንሰላታማ ተራራ የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን ያሳያሉ’ የተባሉ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተጋሩ ይገኛሉ።
በምስሎቹ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ ከሌሎች ሁለት ግለሰቦች ጋር ቆመው ከፊታቸው ደግሞ በርከት ያሉ የጦር መሳሪያዎች ተደርድረው ይታያሉ።
ምስሎቹን “ሰበር መረጃ” በማለት ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ‘ዲጂታል ኢትዮጵያ’ የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገጽ ይገኝበታል።
ይህ ገጽ “ከጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ ዛሬ ብቻ 75 ክላሽ 1ዲሽቃ 2 ብሬን ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተረክቧል” የሚል ጽሁፍም ከምስሎቹ ጋር አጋርቷል።
በተመሳሳይ መልኩ ‘ሀገሬ ሚዲያ’ የሚል ስም ያለው የፌስቡክ ገጽም ምስሎቹን እና የጽሁፍ መረጃውን ያጋራ ሲሆን 35 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በገጹ የተጋራዉን መረጃ መልሰው አጋርተዉታል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ የጉግል ምርት የሆነውና በሰው-ሰራሽ አስተውሎት የተፈበረኩ ምስሎች፣ ቪዲዮ እና ድምጾችን ለማጣራት በሚረዳው ‘SynthID Detector’ በመጠቀም ምስሎቹን መርምሯል።
በዚሁ መሰረት ምስሎቹ ጉግል ኤአይ (Google AI) በመጠቀም የተፈበረኩ መሆኑን ተመልክተናል።
በተጨማሪም ምስሎቹን በምልሰት በመፈለግ (reverse image search) ባደረግነው ማጣራት አንዳንዶቹ ምስሎች ትክክለኛ የሌተናል ጀነራል መሀመድ ተሰማ ምስልን ይዘት በመቀየር የተሰሩ መሆናቸዉን አረጋግጠናል።
ትክክለኛው የጀነራሉ ምስል በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ትክክለኛና የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ ከሁለት ቀናት በፊት የተጋራ ሲሆን በአማራ ክልል የተደረገን ኦፕሬሽን በማስመልከት የተጋራም ነበር፡ https://www.facebook.com/share/p/1BuimH7V2p/?mibextid=wwXIfr
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከምስሉ ጋር ባጋራው የጽሁፍ ‘ምስራቅ ዕዝ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ባደረገው ፀረ-ሽምቅ ስምሪት ፈረስ ቤት ፣ ዋሸራ ፣ ጫት ዋርካ ፣ ሐሙስ ገበያ ፣ ሰከላ እና ሌሎች ቀጣናዎች የነበረው ፅንፈኛ ተደምስሷል’ ብሏል።
የሰው-ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሚፈበረኩ እና ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስል እና ቪዲዮዎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





