የአርሰናል ደጋፊዎች ‘የዶ/ር ዐቢይ ታማኝ ደጋፊ ነን’ የሚል መልዕክት የያዘ ባነር ይዘዉ የተነሱት ፎቶ በሚል እየተጋራ የሚገኝ ምስል በቅንብር የተሰራ ነው

ሰኔ 2፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- ባለፉት ቀናት አርሰናል የ2025/2026 ውድድር ዘመን የእንግሊዙ አርሰናል የእግር ኳስ ክለብ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን በማስመልከት የተለያዩ ዝግጅቶች በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂደዋል።
በዝግጅቶቹም የክለቡ የቀድሞ ተጫዋች ኢማኑኤል ኢቦዬን ጨምሮ የAFTV ሚዲያ አባላት ከክለቡ ደጋፊዎች ጋር ተገናኝተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንድ በቤተመንግስት ሙዝየም ውስጥ የተነሳ ምስል የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ሲሆን መነጋገሪያም ሆኗል።
ይህ ምስል ኢማኑኤል ኢቦዬን፤ የAFTV ሚዲያ አባላት እና ሌሎች ግለሰቦች/ የቡድኑ ደጋፊዎች “ለመሪያችን ዶ/ር ዐቢይና ለክለባችን አርሰናል ታማኝ ደጋፊ ነን” የሚል ባነር ጀርባ ቆመዉ ይታያል።
ምስሉን ካጋሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ‘Wollo Addis’ የተሰኘ የፌስቡክ ገጽ የሚገኝ ሲሆን ገጹ ያጋራውን ምስል ከ50 በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መልሰዉ አጋርተዉታል፣ ከ2 ሸህ በላይ አስተያቶችም ተሰጥተዉበታል።
ኢትዮጵያ ቼክ የዚህን ምስል ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የተለያዩ መገልገያዎችን ተጠቅሟል፣ እንዲሁም በምስሉ ላይ ጥልቅ ምልከታ እና የማመሳከር ስራ ሰርቷል።
በቅድሚያ የተነካኩና ይዘታቸው የተቀየረ ምስሎችን ለመመርመር የሚረዳዉን ፎቶ ፎረንሲክስ ድረ-ገጽ በመጠቀም ባደረግነዉ ማጣራት በምስሉ ዉስጥ የሚገኘውና “ለመሪያችን ዶ/ር ዐቢይና ለክለባችን አርሰናል ታማኝ ደጋፊ ነን” የሚል ጽሁፍ የያዘው ባነር በቅንብር የተካተተ መሆኑን የሚያሳይ ትንተና አግኝተናል።
በተጨማሪ ‘illuminarty.ai’ የተሰኘዉን ድረ-ገጽ በመጠቀም በባነሩ ላይ ባደረግነዉ ምርመራ ባነሩ በሰው-ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰራ መሆኑን (88%) የሚያሳይ መረጃ አግኝተናል።
በሌላ በኩል ምስሉን በማግዘፍ ባደረግነው ጥልቅ ምርመራ ባነሩን ይዘው የሚታዩ እጆች ቅርጻቸው የተዛባ እና ትክክለኛ ያልሆኑ መሆናቸውን ተመልክተናል።
በተጨማሪም በምስሉ በስተቀኝ ዳር ላይ የቆመ ግለሰብ የእጅ ጌጥ ምስሉ በመነካካቱ ይዘቱ የተቀየረ መሆኑን ተመልክተናል።
ኢትዮጵያ ቼክ በእለቱ የተነሱ እና የተቀረጹ ምስሎች እና ቪዲዮችን በመመልከትም የማመሳከር ስራ ሰርቷል።
በቤተመንግስት ሙዝየም የተነሳውና ትክክለኛ ፎቶ ላይ በስተግራ ጥግ የሚገኝ ግለሰብ የታችኛው የእግር ክፍል ‘I love Addis Ababa’ በሚለው የፎቶ ፍሬም የተደበቀ ነው።
ነገር ግን “ለመሪያችን ዶ/ር ዐቢይና ለክለባችን አርሰናል ታማኝ ደጋፊ ነን” የሚል ጽሁፍ የያዘው ባነር ላይ ግለሰቡ ጥቁር ቆዳ መሳይ ጫማ ተጫምቶ ይታያል።
ኢትዮጵያ ቼክ የግለሰቡን የእለቱን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች የተመለከተ ሲሆን ግለሰቡ በእለቱ የተለያዩ ቀለማት ያለው ስኒከር ጫማ ተጫምቶ እንደነበር ተመልክቷል።
ይህም ባነሩ ያለበት ምስል ከትክክለኛው ምስል ላይ ‘I love Addis Ababa’ ሚለውን የፎቶ ፍሬም በማጥፋት በምትኩ የግለሰቡ የታችኛው የእግር ክፍል ላይ በሰው-ሰራሽ ክህሎት ሀሰተኛ ጫማ የተካተተ መሆኑን አረጋግጠናል።
በዚሁ መሰረት ከላይ የተዘረሩትን ቴክኖሎጂን እና የባለሙያ ምልከታን በመጠቀም ባደረግነዉ ማጣራት “ለመሪያችን ዶ/ር ዐቢይና ለክለባችን አርሰናል ታማኝ ደጋፊ ነን” የሚል ጽሁፍ የያዘው ባነር ትክክለኛ ያለሆነ እና በቅንብር የተካተተ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።
ትክክለኛ ምስሎች ላይ የተፈበረኩ ይዘቶችን በመጨመር የሚጋሩ መልዕክቶች ለሀሰተኛ እና የተሳሳተ መረጃ ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





