ትናንት ምሽት መቀሌ ከተማ ውስጥ የተሰማውን የፍንዳታ ድምፅ ተከትሎ የተሰራጨው ምስል አሳሳች ነው

የካቲት 7፣ 2018
/ኢትዮጵያ ቼክ/- ትናንት ምሽት 3:30 ገደማ መቀሌ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ መሰማቱን ተከትሎ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
አንዳንዶች ፍንዳታው የድሮን ጥቃት እንደሆነ ሲገልፁ ሌሎች ደግሞ የፈንጂ ድምፅ እንደነበር መላምት ሲያስቀምጡ ታይተዋል።
‘Gamo ArbaMinch’ የተባለ እና ከ144 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ በዚህ ዙርያ በሰበር ዜና መረጃ ያሰራጨ ሲሆን “በመቀሌ፣ ትግራይ ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰምቷል፣ የፍንዳታው ምክንያት እስካሁን አልተረጋገጠም፣ የተጎዱ ሰዎች ወይም የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩም የተረጋገጠ መረጃ የለም” ብሏል።
በተመሳሳይ ‘East African Insider’ የተባለ እና መረጃዎቹን በእንግሊዝኛ የሚያቀርብ ከ53 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው የፌስቡክ ገፅ ይህንኑ ምስል በፅሁፍ አቀናብሮ በመልቀቅ በርካታ ግብረ-መልስ አግኝቷል።
ገፁ ከዚህ መረጃ ጋር አንድ ከፍተኛ ፍንዳታን የሚያሳይ ምስል የተጠቀመ ሲሆን ምስሉ ብዙዎች ዘንድ ስጋትን እና ጥርጣሬን ጭሯል።
ሚድያችን በዚህ ዙርያ ባደረገው ማጣራት የተባለው ፍንዳታ መከሰቱን ያረጋገጠ ሲሆን ምስሉ ግን ከሌላ ሀገር የተወሰደ መሆኑን ተመልክተናል። ምስሉ ከአመት በፊት እስራኤል ጋዛ ላይ ጥቃት ስታደርስ እንደሚያሳይ መረጃዎች ያሳያሉ።
በቢዝነስ ካምፓስ አጥር አቅራቢይ የተከሰተው ፍንዳታ ምክንያቱ ምን እንደሆነ የመቀሌ ፖሊስ እያጣራ መሆኑን የሚገልፁ መረጃዎች ወጥተዋል። ፍንዳታው በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት አለማድረሱን የከተማው ሰላምና ፀጥታ ፅ/ቤት ለመቐለ ኤፍ ኤም ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ቼክ
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::





