ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ሴናተር ክሩዝ የኢትዮጵያን ካርታ ሲያነቡ የሚያሳየው ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ሴናተር ክሩዝ የኢትዮጵያን ካርታ ሲያነቡ የሚያሳየው ምስል በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተፈበረከ ነው

ጥር 1፣ 2018

የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ሴናተር ቴድ ክሩዝ የኢትዮጵያን ካርታ ሲያነቡ የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋራ ይገኛል። በምስሉ ላይ ሴናተሩ ከኢትዮጵያ ካርታ ላይ የሶማሊ ክልልን በእጃቸው እየነኩ ለፕሬዝዳንቱ ሲያሳዩ ይታያል።

ይህን ምስል ያጋሩ የፌስቡክ ገጾች እና አካውንቶች ምስሉን ከሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና እንዲሁም ሰሞኑን በአሜሪካ እና ቬኔዙዌላ መካከል ከተፈጠረዉ ሁኔታ ጋር በማያያዝ አጋርተዋል።

በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎችም ምስሉን በተመለከተ የተለያዩ ሀሳብ እና አስተያየቶችን እየሰጡ መሆኑንም ተመልክተናል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ በምስሉ ላይ ባደረገዉ ማጣራት ምስሉ ትክክለኛ እንዳልሆነ እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሰራ እንደሆነ አረጋግጧል።

የምስሉን ትክክኛነት ለማጣራት የጉግል ምርት የሆነዉን ሲንት አይዲ ዲቴክተር (SynthID Detector) የተጠቀምን ሲሆን ምስሉ በጉግል ኤአይ (Google AI) የተሰራ እንደሆነ ተመልክተናል።

በተጨማሪም ምስሉ የሀገራት እና የባህረ ሰላጤ ስም ጽሁፍ ግድፈቶች ያሉበት መሆኑ እንዲሁም በካርታዉ ቀኝ የታችኛዉ ክፍል የሚገኘው የካርታዉ ቁልፍ (map key/legend) ላይ ያለው ጽሁፍ ትርጉም አልባ እና በAI ምስሎች ላይ በስፋት የሚታይ ስህተት በመሆኑ ምስሉ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው።

ይህ ምስል በአንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ከመሰራጨቱ ውጪ በሌሎች አለም አቀፍ ሚድያዎች ወይም በመንግስታዊ ተቋማት በየትኛውም ግዜ ቀርበው እንደማይገኙም ተመልክተናል፣ ይህም ምስሉ በቅንብር የተሰራ እና እውነታን የማያሳይ ሌላ ጠቋሚ ምልክት ሆኗል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተፈበረኩ እንዲሁም ከሌላ ቦታ ተወስደው ከአውድ ውጭ የሚጋሩ ምስሎች ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች ሊያጋልጡን ስለሚችሉ ከማመናችን እና መልሰን ከማጋራታችን በፊት ተገቢዉን ማጣራት እናድርግ።

ኢትዮጵያ ቼክ

ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ

    ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::