በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‘የሞሐመድ ጋዳፊ የልጅ ልጅ’ ተብለው የቀረቡት ግሰብ የቀድሞው የሊቢያ መሪ ዘመድ አይደሉም

ታህሳስ 3፣ 2018
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዛሬው ዕለት የቀድሞው የሊቢያ መሪ የሞሐመድ ጋዳፊ የልጅ ልጅ በኢትዮጵያ ተገኝተው አንድ ንግግር እንዳደረጉ መረጃ አጋርቶ ነበር።
“ሙሳ ኢብራሂም ጋዳፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ለነጻነቱ መታገሉ በመላው አፍሪካ ያሉ የነጻነት ንቅናቄዎችን ማነሳሰቱን ሙሳ ኢብራሂም ጋዳፊ ገለጹ” የሚል መረጃ በመንግስታዊው የፕሬስ ድርጅት ተሰራጭቷል።
ሚድያው አክሎም “ሙሳ ኢብራሂም ጋዳፊ ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ለነጻነቱ በመታገል በመላው አህጉር ያሉ የነጻነት ንቅናቄዎችን አነሳስቷል” ብሏል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ቼክ በጉዳዩ ዙርያ ባደረገው ማጣራት ሙሳ ኢብራሂም ጋዳፊ የቀድሞው የሊቢያው መሪ የልጅ ልጅ እንዳልሆኑ አረጋግጧል።
ንግግሩን ተናገሩት የተባሉት እ.አ.አ በ2011 የጋዳፊ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ሆነው ተሹመው እስከ ጋዳፊ መውደቅ ያገለገሉት ሙሳ ኢብራሂም ናቸው።
ሙሳ ኢብራሂም በሊቢያ ጦርነት ወቅት ተከታታይ መግለጫዎችን ለጋዜጠኞች በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን የኮሎኔል ጋዳፊ መንግስት ከወደቀ በኋላ ግን ረዘም ላለ ግዜ ደብዛቸው ጠፍቶ ነበር። ከዛም ግብፅ እንደተገኙ፣ ግብፅ ለሊብያ አስተላልፋ እንደሰጠቻቸው፣ ሙሳ ኢብራሂም በስተመጨረሻም ከሊብያ እስር አምልጠው ወደ ሰርቢያ መሄዳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህም መሰረት ግለሰቡ የጋዳፊ የልጅ ልጅ ናቸው ተብሎ የቀረበው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
ትልልቅ ሚድያዎች የሚያሰራጩዋቸው መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ሳያረጋግጡ ሲያጋሩ ተአማኒነታቸውን ከመቀነሱ በላይ በርካታ ህዝብን ያሳስታሉ።
ኢትዮጵያ ቼክ!
ወቅታዊ መረጃዎችን ቀጥታ በኢሜልዎ ለማግኘት ይመዝገቡ
ያቀረቡትን የግል መረጃ በግላዊ መመሪያችን መሠረት እንጠብቃለን::
